የላሊበላ ገዳም ቋሚ ገቢ እንዲኖረው የሚያስችል እንቅስቃሴ ተጀመረ

ሚያዝያ 15/2014 (ዋልታ) የላሊበላ ገዳም ቋሚ የገቢ ምንጭ እንዲኖረው ለማድረግ እንቅስቃሴ መጀመሩ ተገለጸ፡፡

የድጋፍ አሰባሳቢ ኮሚቴ አስተባባሪ ዲያቆን አንተነህ እሸቱ እንደገለጹት የላሊበላ ገዳም ወደነበረበት ለመመለስ በዘላቂነት መፍትሔ የሚሆነው በተቻለ ፍጥነት የሀገርን ሰላም እና የቱሪዝም ፍሰቱን ወደነበረበት መመለስ ነው።

ግሸን በዓመት እስከ አንድ ሚሊየን ዜጎች እንደሚጎበኙት የጠቆሙት አስተባባሪው በላሊበላም የሀገር ውስጥ የቱሪዝም እንቅስቃሴውን ለማነቃቃት እንዲሁም ደብሩ መሰል ችግር ሲገጥመው መቋቋም የሚችልበት ቋሚ የገቢ ምንጮችን በሂደት ለመመስረት መታሰቡን አመላክተዋል።

አስራ አንድ አብያተ-ክርስቲያናትን አቅፎ የያዘው ላሊበላ በውስጡ ከአንድ ሺሕ በላይ አገልጋይ ካህናት፣ ከ100 በላይ የቅርስ ጠባቂዎች እንዲሁም በላሊበላ ከተማ ልመና እንዲቀር ለማድረግ ያደራጃቸውና ከደብሩ በቀጥታ የሚደጎሙ አረጋዊያን ተጧሪዎች፣ ሕጻናት ከነወላጆቻቸው በድምሩ ከ10 ሺሕ በላይ በቀጥታ በገዳሙ የሚደጎሙ ዜጎች መኖራቸውንም አንስተዋል፡፡

ገዳሙ ቀደም ሲል ለካህናትና ቅርስ ጠባቂዎች ደመወዝ፣ ለሚያስተዳድራቸው አረጋዊያን እና ሕጻናት ድጋፍ የሚያስፈልገውን አራት ሚሊየን ብር ወርሃዊ ወጪውን ሸፍኖ በዙሪያው ላሉ የገጠር አብያተ-ክርስቲያናትና ለአካባቢው ማኅበረሰብ ሲደግፍ እንደነበር አስታውሰዋል።

ሰሞኑን በተደረገው የድጋፍ ማሰባሰብ ፕሮግራም ስምንት ሚሊየን የሚሆን ብር ቃል መገባቱን አስታውሰው ነገር ግን ከሁለት ወር የዘለለ የደመወዝ ወጪ መሸፈን የማይችል በመሆኑ ዘላቂ ድጋፍ መመስረት እንደሚገባ አመላክተዋል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ሰላምታ መጽሔት ላይ የላሊበላ ፎቶ ሳይወጣ የቀረበት ጊዜ የለም ያሉት አስተባባሪው ላሊበላ ሃይማኖታዊ ብቻ ሳይሆን ዓለም ዐቀፍ ቅርሰ ጭምር በመሆኑ ሊረሳ አይገባም ብለዋል።

የላሊበላ ዓለም ዐቀፍ ቅርስ የኢትዮጵያ አየር መንገድን ጨምሮ የሆቴሎች፣ ባንኮችና የተለያዩ ተቋማት የገቢ ምንጭ በመሆኑ ገዳሙን ባለበት ለማቆየት የመጀመሪያውን እሳት በማጥፋት በኩል ሁሉም ሊረባረቡ ይገባል ማለታቸውን ኢፕድ ዘግቧል።

የሮሃ ቅዱስ ላሊበላ ገዳም የገቢ ማሰባሰቢያ በኢትዮጵያ ንግድ ባንከ፣ አቢሲንያ ባንክ፣ ዳሸን ባንክ እና ሕብረት ባንኮች በተመሳሳይ ባለ አራት ዲጂት የባንክ ሂሳብ ቁጥር 0712 ድጋፍ እንዲደረግ የተመቻቸ መሆኑን ጠቁመዋል።

ለፈጣን መረጃዎች፦
ፌስቡክ https://bit.ly/3Ma7QTW
ቴሌግራም https://t.me/WALTATVEth
ዩቲዩብ https://www.youtube.com/c/WaltaTV/featured
ቲዊተር https://twitter.com/walta_info
አብራችሁን ስለሆናችሁ እናመሰግናለን!