የሕወሓት አሸባሪ ቡድን በአፋር ክልል 240 ንጹሃን ዜጎችን ገድሏል- አልጀዚራ

ነሐሴ 3/2013 (ዋልታ) – የሕወሓት አሸባሪ ቡድን በአፋር ክልል በፈጸመው ጥቃት 107 ሕጻናትን ጨምሮ 240 ንጹሃን ዜጎችን መገደላቸውን አልጀዚራ ዘገበ።

መንግሥት ምንም እንኳን የተናጠል የተኩስ አቁም ቢያደርግም አሸባሪው ሕወሓት በአጎራባች ክልል የሚያደርገውን ጥቃት ቀጥሎበታል ብሏል በዘገባው።

በኢትዮጵያ በቅርቡ ጉብኝት ያደረጉት የአሜሪካው ዓለም አቀፍ ልማት ኤጀንሲ (ዩ ኤስ ኤድ) ኃላፊ ሳማንታ ፓወርም የሕወሓት ወታደራዊ እንቅስቃሴ እንዳሳሰባቸው መናገራቸውን አስታውሷል።

የሽብር ድርጊቱን ተከትሎ በአፋርና አማራ ከልሎች የሚኖሩ በርካታ ሰዎች ከቀያቸው እንዲፈናቀሉ ማድረጉን ኃላፊዋ ተናግረው ነበር።

አልጀዚራ እንደዘገበው ቡድኑ የፈጸመው ጥቃት በአፋር ክልል “ካሊኩማ” በሚባል ሥፍራ የሚገኙ ከተማዎችና ትምህርት ቤቶች ላይ ያነጣጠረ ነበር።

በዚህም 107 ሕጻናትን ጨምሮ በድምሩ 240 ንጹሃን ዜጎች መገደላቸውንና ይህንን የሽብር ጥቃት ተከትሎ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎች መፈናቀላቸው በዘገባው አመልክቷል።

አሸባሪ ቡድኑ በአፋር ክልል ላካሄደው የሽብር ጥቃት ሕፃናትን ማሰለፉንም አልጀዚራ በዘገባው አካቷል።
በመንግስት የተናጠል የተኩስ አቁም ከተደረገ በኋላ የአሸባሪ ቡድኑ የአገሪቷን ሠላምና ደኅንነት እያወከ መሆኑን ዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ እንዲገነዘብ መንግሥት ጥሪ ማቅረቡን ዘገባው አስታውሷል።