የመንግሥት የልማት ድርጅቶች ይዞታና አስተዳደር 271.3 ቢሊዮን ብር ገቢ መሰብሰቡን አሰታወቀ

መጋቢት 14/2014 (ዋልታ) የመንግሥት የልማት ድርጅቶች ይዞታና አስተዳደር በበጀት ዓመቱ ባለፉት ስድስት ወራት ከምርት ሽያጭና አገልግሎት 271 ነጥብ 3 ቢሊዮን ብር ገቢ መሰብሰቡን አሰታወቀ።
የየመንግሥት የልማት ድርጅቶች ይዞታና አስተዳደር ዋና ዳይሬክተር ሀብታሙ ኃይለሚካኤል የግማሽ ዓመቱን የሥራ አፈጻጸም አስመልክቶ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ እንዳስታወቁት የልማት ድርጅቶች በግማሽ ዓመቱ 263 ነጥብ 3 ቢሊዮን ብር ገቢ ለመሰብሰብ ታቅዶ 271 ነጥብ 3 ቢሊዮን ብር ገቢ ተገኝቷል።
ከጠቅላላ ገቢው በዘርፍ ደረጃ 56 በመቶው ከትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ፣ 23 ነጥብ 4 ከፋይናንስ እና 10 ነጥብ 4 ከኮሙዩኒኬሽን ዘርፍ መሆኑን ገልጸው ይህም የእቅዱን 101 ነጥብ 6 መሆኑን ያሳያል ብለዋል፡፡
ውጤቱ የተመዘገበው ልማት ድርጅቶች የማምረት አቅማቸውና የአገልግሎት አሰጣጣቸው በማዘመናቸው የመጣ ውጤት እንደሆነና ድርጅቶቹ ከሀብት አባካኝንት ወደ ሀብት ፈጣሪነት መሸጋገራቸው አንዱ ለውጤቱ ስኬታማነት ጉልህ አስተዋጽኦ እንደነበረው አክለዋል።
በአስተዳደሩ ስር 36 የልማት ድርጅቶች የሚገኙ ሲሆን 32 ትርፋማ ሲሆኑ አራቱ ኪሳራ ገጥሟቸዋልም ብለዋል።
የልማት ድርጅቶቹ የውጭና የውስጥ የብድር እዳ አከፋፈል አቅማቸው ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ መጥቷል ያሉት ዳይሬክተሩ አስተዳደሩ በግማሽ ዓመቱ ለ12 ሺሕ 260 ዜጎች የሥራ እድል እንደፈጠረና ከነዚህም 22 በመቶ የሚሆኑት ሴቶች እንደሆኑ መግለፃቸውን የኢፕድ ዘገባ አመላክቷል።