የመንግስት ኮሙኒኬሽን በክረምቱ ለአደጋ ተጋላጭ አካባቢዎች ለሚኖሩ ዜጎች የጥንቃቄ መልዕክት አስተላለፈ


ሐምሌ 22/2016 (አዲስ ዋልታ) የመንግስት ኮሙኒኬሽን ለአደጋ ተጋላጭ በሆኑ አንድ አንድ አካባቢዎች ለሚኖሩ ዜጎች የጥንቃቄ መልዕክት አስተላለፈ።

ከክረምቱ ዝናብ ጋር ተያይዞ በአንድ አንድ የሃገራችን አካባቢዎች በደረሱ የመሬት መንሸራተትና የዉሃ ሙሌት ምክንያት የበርካታ ዜጎቻችን ሕይወት አልፏል፤ የአካል ጉዳትና የንብረት መውደም ደርሷል፡፡

በትናንትናው ምሽት በሲዳማ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ማዕከላዊ ሲዳማ ዞን ወንሾ ወረዳ ግሽሬ ጉዱ ሞና ሆሞ ተብሎ በሚጠራ አካባቢ በጣለው ከፍተኛ ዝናብ ምክንያት በተከሰተው የመሬት መንሸራተት አደጋ የ6 (ስድስት) ሰዎች ሕይወት አልፏል፡፡ የአካል ጉዳትና የንብረት መውደም አደጋም ደርሷል፡፡

በተጨማሪም በአማራ ብሔራዊ ክልላዊ መንግሥት ከዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አስተዳደር ስሃላ ሰየምት ወረዳ ወደ ዝቋላ ወረዳ በተከዜ ወንዝ በጀልባ ሲጓዙ በነበሩት ሰዎች ላይ በውሃ ሙሌት ምክንያት በደረሰው አደጋ የሰው ሕይወት አልፏል፡፡

በመሆኑም የኢትዮጵያ ፌዴራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ መንግሥት በደረሱ አደጋዎች ሳቢያ ለተጎዱ ዜጎች የተሰማውን ጥልቅ ኀዘን ይገልጻል፡፡ ለቤተሰቦቻቸውና ወዳጅ ዘመዶቻቸው መፅናናትን ይመኛል፡፡

ህብረተሰቡ ወቅቱ የክረምት ወቅት መሆኑን በመገንዘብ ለመሰል አደጋዎች ተጋላጭ በሆኑ አካባቢዎች የሚኖሩ ዜጎች አስፈላጊውን ጥንቃቄ እንዲያድርጉ መንግሥት ያሳስባል፡፡