የመጀመሪያው የሳይንስ ካውንስል የምክክር መድረክ ተካሄደ

የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር “ሳይንስ ለኢትዮጵያ ልማትና ብልፅግና” በሚል መሪ ቃል የመጀመሪያው የሳይንስ ካውንስል የምክክር መድረክ አካሂዷል፡፡

የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስትር ዴኤታ ፕሮፌሰር አፈወርቅ ካሱ በሃገሪቱ የሳይንስ ልማትን ለማስፋፋት እና ውጤት ለማምጣት ከተቋማት ጋር በቅንጅት መስራት ጠቃሚ መሆኑን ገልጸው፣ ኢትዮጵያ ያቀደችውን የ10 አመት የልማት እቅድ ውጤታማነት ለማረጋገጥ ከሳይንስ ዘርፉ ጋር በቅንጅት መስራት ያስፈልጋል ብለዋል፡፡

በመድረኩ በእንግድነት የተገኙት የጠቅላይ ሚንስትሩ የማህበራዊ ዘርፍ አማካሪ ሚንስትር ፕሮፌሰር ሂሩት ወ/ማርያም ሳይንስ ተፈጥሮን፣ አለማችንን እንዲሁም አከባቢያችንን የምንገልፅበትና የምንረዳበት መንገድ እንደመሆኑ ወጣቶችን በሳይንስና ቴክኖሎጂ በማሰልጠን ለሳይንሳዊ ጥናትና ምርምሮች፣ ለፈጠራና ችግር ፈቺ ጥናቶች መጠቀም እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡

ፕሮፌሰር ሂሩት ወ/ማርያም

በአለም ዙሪያ የሚከሰቱ ችግሮችን እና እክሎችን ከመቅረፍ አኳያ ሳይንስ የሚያበረክተው አስተዋፅኦ ከፍተኛ መሆኑን ከተለያዩ ሃገራት ተሞክሮ መውሰድ እንችላለን ያሉት ፕሮፌሰር ሂሩት፣ ኢትዮጵያም በሳይንስና ቴክኖሎጂ ዘርፍ በርካታ የቤት ስራ ይጠበቅባታል ብለዋል፡፡

የሳይንስ ዘርፉን ውጤታማ በማድረግ ረገድ አሉ የተባሉትን ተግዳሮቶች በማንሳት አንዱና ዋነኛው የትብብርና ቅንጅት ስራዎች አለመኖርና አለመጠናከር መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

በመድረኩም  ሳይንስ ለሃገር እድገትና ብልፅግና ያለው ፋይዳ ዙሪያ በምሁራን ጥናታዊ ፅሁፍ ቀርቦ ውይይት ተደርጓል፡፡

(በአመለወርቅ መኳንንት)