የመጀመሪያው የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ታለንት ልማት ኢንስቲትዩት ባለሙያዎችን ማሰልጠን ጀመረ

ሰኔ 14/2014 (ዋልታ) በኢትዮጵያ የመጀመሪያ የሆነው የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ታለንት ልማት ኢንስቲትዩት ግንባታ ተጠናቆ የተመረጡ የፈጠራ ባለሙያዎችን ተቀብሎ ማሰልጠን ጀመረ፡፡
የኢኖቬሽን እና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴር የኢንስቲትዩት ግንባታ መጠናቀቁን አስመልክቶ ለምረቃ በዓል የሚሆኑ የፈጠራ ሞዴል ሥራዎችን የሚያቀርቡ የተመረጡ የፈጠራ ባለሙያዎችን በተቋሙ ተቀብሎ ድጋፍ በማድረግ ሥራዎቻቸውን እንዲያበለፅጉ እየሰራው ነው ብሏል፡፡
እንዲሁም የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር ደኤታ ባይሳ በዳዳ ከፈጠራ ባለሙያዎች ጋር መክረዋል።
ሚኒስትር ዴኤታው ችግር ፈቺ የፈጠራ ሥራዎችን በመስራት በሀሳብ የተጀመረውን ወደ ውጤት በመቀየር በቀጣይ ቅበላ ለሚደረግላቸው የልዩ ተሰጦና ተውቦ ተማሪዎች ሞዴል የሚሆኑ ሥራዎችን ይዘው መቅረብ እንዳለባቸው የፈጠራ ባለሙያዎችን አሳስበዋል፡፡
“አይቻልም” የሚባሉ ሥራዎች እንደሚቻሉ ማሳየት የምንችልበትን ሂደት በመፍጠር የፈጠራ ውጤቶችን ወደ ሀብት በመቀየር፣ የተክኖሎጂ ሽግግርን በማሳለጥ፣ ሀገር በቀል ቴክኖሎጂዎችን በማዘመን፣ የሥራ እድል በመፍጠርና ከውጪ የሚገቡ ቴክኖሎጂዎችን በራሳችን በመተካት የድህነትን ጊዜ ልናሳጥር ይገባልም ብለዋል፡፡
የተመረጡት የፈጠራ ባለሙያዎች በስፔስ ቴክኖሎጂና ጂኦስፓሻል እንዲሁም በእንጦጦ ኦብዘርቫቶሪ የምርምር ተቋማት ጉብኝት አድርገዋል።
የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ታለንት ልማት ኢንስቲትዩት ፕሮጀክት ፅህፈት ቤት ኃላፊ ሂርፓሳ ጫላ የፈጠራ ባለሙያዎችን በመደገፍ የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ውጤቶች ባለቤት መሆን የሚያስችለንን ሥራ እንሰራለን ብለዋል።
የተቋሙ ሥራ መጀመር በሀገር አቀፍ ደረጃ ያሉ ልዩ ተሰጥኦ ያላቸውን በመሰብሰብ፣ በማብቃት፣ ወደ ውጤት በመቀየርና የሥራ ዕድል በመፍጠር ኢትዮጶያ ያላትን ብዙ የወጣት ሀይል ሀብት መጠቀም የሚቻልበትን ስርዓት ይፈጥራል ተብሏል፡፡
የፈጠራ ባለሙያዎቹ ከጉብኝቱ ብዙ ነገር እንዳገኙ ጠቅሰው እየተደረገላቸው ያለው ድጋፍ አቅም ከመፍጠሩም ባለፈ ስራቸውን ወደ ውጤት መቀየር እንደሚያስችላቸው መግለጻቸውን የሚኒስቴሩ መረጃ ያሳያል፡፡