የመገናኛ ብዙሃንና ኮሚዩኒኬሽን ባለሙያዎች ህዝብን በሚያቀራርቡ ጉዳዮች ላይ እንዲያተኩሩ ተጠየቀ

የመገናኛ ብዙሃንና ኮሙኒኬሽን ባለሙያዎች ህዝብን ከህዝብ የሚያቃቅርና የሚያራርቅ ሳይሆን ሊያቀራርቡ በሚችሉ ጉዳዮች ላይ አተኩረው እንዲሰሩ ተጠየቀ።

የተፈናቀሉ ወገኖችን ለመደገፍና ለማቋቋም የሚዲያ፣ ህዝብ ግንኙነትና ኮሙኒኬሽን ሚና በሚል መሪ ሃሳብ ዛሬ በባህርዳር ከተማ የውይይት መድረክ ተካሂዷል።

የአማራ ክልል መንግስት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት ዋና ዳይሬክተር አቶ ግዛቸው ሙሉነህ  በመድረኩ እንደተናገሩት፤ የመገናኛ ብዙሃንና ኮሙኒኬሽን ባለሙያዎች  ህዝብን ከህዝብ የሚያቀራርቡ ትክክለኛ መረጃዎችን ለህብረተሰቡ ማድረስ አለባቸው።

“ህዝብን ለግጭት የሚያነሳሱ መረጃዎችን የሚያሰራጩ የማህበረሰብ አንቂዎችን ተቀናጅተን ልንታገላቸው ይገባል” ያሉት አቶ ግዛቸው፤ የመገናኛ ብዙሃንና ኮሙኒኬሽን ባለሙያዎች የሚያቀራርብ መረጃ ለህብረተሰቡ እንዲያደርሱ ጠይቀዋል።

ይህም በንጸሃን ዜጎች  ላይ የሚደረስ ጥቃትና መፈናቀል በመቀነስ ኢትዮጵያ የቀደመ አንድነቷ ተጠብቆ የህዝቦች አንድነትና ወንድማማችነት እየጠነከረ እንዲሄድ እንደሚያግዝ  ተናግረዋል።

ከቤት ንብረታቸው ተፈናቅለው የሚገኙትን ጨምሮ የዕለት ደራሽ እርዳታ የሚያስፈልጋቸው ዜጎች በክልሉ  በብዛት እንዳሉ ገልጸው፤ “ለነዚህ ወገኖች ድጋፍ የማሰባሰቡን ስራ አጠናክረን መቀጠል ይኖርብናል” ብለዋል።

የመገናኛ ብዙሃንና የኮሙኒኬሽን ባለሙያዎች ከቤት ንብረታቸው የተፈናቀሉ ዜጎች ወደቀያቸው እንዲመለሱ መንግስት የጀመረውን ጥረት ማገዝ እንዳለባቸውም አስገንዝበዋል።

“የተዛቡ አመለካከቶችን በማረም ለላቀ የህዝብ ተጠቃሚነት ቅድሚያ ሰጥተን ልንሰራ ይገባል” ያሉት ደግሞ የክልሉ አደጋ መከላከልና ምግብ ዋስትና ፕሮግራሞችና ልዩ ድጋፍ የሚሹ አካባቢዎች ማስተባበሪያ ኮሚሽን የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ እያሱ መስፍን ናቸው።

በማንነት፣ ግጭትና በህግ ማስከበር ዘመቻው ከተለያዩ ክልሎች ተፈናቅለው በአማራ ክልል በመጠለያ ጣቢያዎችና ከዘመድ ጋር ከ277 ሺህ በላይ ወገኖች እንደሚገኙ ገልጸዋል።

“እነዚህ ወገኖች ከፌዴራል መንግስት የሚላከውን ጨምሮ ከክልሉ መንግስት፣ ህብረተሰቡ፣ ባለሃብቶችና ረጂ ድርጅቶች የዕለት ምግብ እርዳታ እየቀረበላቸው ይገኛል” ብለዋል

ለነዚህ ወገኖችም በየወሩ ከ42 ሺህ ኩንታል በላይ የምግብ እህል ኮሚሽኑ እያቀረበ እንደሚገኝም ጠቅሰዋል።

አቶ እያሱ እንዳሉት፤ የተፈናቃይ ቁጥር በየጊዜው መጨመር፣ የጠራ መረጃና ቅንጅታዊ አሰራር አለመኖር፣ የድጋፍ መዘግየትና የተዛቡ ዘገባዎች በድጋፍ አሰጣጡ የተስተዋሉ ችግሮች መሆናቸውን ኢዜአ በዘገባው አስታወቋል፡፡