የመገጭ ግድብ በተያዘለት ጊዜ ተጠናቆ የመጠጥ ውሃ ችግር እንዲፈታ መንግስት በገባው ቃል መሠረት ለፍጻሜ ያበቃል


ሐምሌ 12/2016 (አዲስ ዋልታ) የመገጭ መስኖና መጠጥ ውሃ ግድብ ፕሮጀክት በተያዘለት ጊዜ ተጠናቆ የጎንደር ከተማን ህዝብ የመጠጥ ውሃ ችግር በዘላቂነት እንዲፈታ መንግስት በገባው ቃል መሠረት ለፍጻሜ ያበቃል ሲሉ የገንዘብ ሚኒስትር አህመድ ሽዴ ገለጹ።

ሚኒስትሩ የመገጭ መስኖና መጠጥ ውሃ ግድብ ፕሮጀክት የግንባታ እንቅስቃሴን ዛሬ ጎብኝተዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በሰጡት አመራር የፕሮጀክቱን ግንባታ የተረከበው አዲሱ ሥራ ተቋራጭ የግድቡ ግንባታ በተያዘለት የጊዜ ገደብ እንዲጠናቀቅ አቅጣጫ ተቀምጦ ርብርብ እየተደረገ ነው።

በተሰጠው አቅጣጫ መሰረትም የሥራ ተቋራጩ በአጭር ጊዜ ውስጥ ወደ ስራ እንዲገባ የገንዘብ ሚኒስቴር በጀት በወቅቱ በመልቀቅ ድጋፍ ማድረጉ ተገልጿል።


የግድቡ ተቋራጭ አማካሪ መሃንዲስ ወርቅነህ አሰፋ በበኩላቸው ተቋራጩ ግንባታውን በተያዘለት ጊዜ ሰርቶ ለማጠናቀቅ በቀን ለ20 ሰዓታት እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

በአሁኑ ወቅት የግድቡ ግንባታ 57 በመቶ መድረሱን ጠቁመው በ2018 ዓ.ም ግንባታውን ለማጠናቀቅ እንደታቀደ መናገራቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

ግድቡ ሲጠናቀቅ ከሚይዘው ውሃ 30 በመቶው ለጎንደር ከተማ የመጠጥ ውሃ የሚውል ሲሆን 17 ሺሕ ሄክታር መሬትም በመስኖ የማልማት አቅም ይኖረዋል። ግድቡ 185 ቢሊዮን ሜትር ኪዩብ ውሃ የመያዝ አቅም እንዳለው ታውቋል።

በጉብኝቱ የገንዘብ ሚኒስቴር የሥራ ባልደረቦች የጎንደር ከተማ ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ባዩህ አቡሃይ እንዲሁም የከተማው አመራር አባላት ተሳትፈዋል።