የሚኒስትሮች ምክር ቤት በአራት ጉዳዮች ላይ ተወያይቶ ውሳኔ አሳለፈ

 

ግንቦት 13/2014 (ዋልታ) የሚኒስትሮች ምክር ቤት በዛሬው ዕለት ባካሄደው 8ኛ መደበኛ ስብሰባ በአራት ጉዳዮች ላይ ተወያይቶ ውሳኔ አሳለፈ፡፡

ምክር ቤቱ በመጀመሪያ ደረጃ የተወያየው የፌደራል መንግስቱ አስፈጻሚ ተቋማት ከተሰጣቸው ስልጣንና ተግባራቸው ጋር የሚመጣጠን የሰው ሃይል እንዲኖራቸው የሚያስችል የአደረጃጀት ማሻሻያ በማድረጋቸው በቀጣይ ሊፈጸሙ የሚገባቸው አቅጣጫዎች በተመለከተ በሲቪል ሰርቪስ ኮምሽን የቀረበው የውሳኔ ሃሳብ ላይ ተወያይቶ በሙሉ ድምጽ አጽድቋል፡፡

በሁለተኛ ደረጃ የሚኒስቴሮች ምክር ቤት የተወያየው በኢንቨስትመንት ማበረታቻ ረቂቅ ደንብ ነው፡፡ ደንቡ የኢንቨስትመንት ማበረታቻዎች ለታለመለት ዓላማ መዋሉን ለማረጋገጥ የሚያስችል የክትትል ሥርዓት እንደሚዘረጋ በሚያስችል መልኩ ውይይት ከተደረገበት በኋላ በነጋሪት ጋዜጣ ታትሞ ከወጣበት ቀን ጀምሮ በስራ ላይ እንዲውል ምክር ቤቱ ወስኗል፡፡

በሶስተኛ ደረጃ ምክር ቤቱ የተወያየው በጉምሩክ ረቂቅ ደንብ ላይ ነው፡፡ ምክር ቤቱ ደንቡ የጉምሩክ መጋዘን አስተዳደርን እና የጉምሩክ አስተላላፊዎችን በሚመለከት የወጡ ደንቦችን በአንድ በማጠቃለል ፣ የማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ ልማት የሚደግፍ እና ሕጋዊ ንግድን እና ኢንቨስትመንትን የሚያበረታታ፣ በስራ ላይ ካለው የጉምሩክ አዋጅ ጋር የሚጣጣም ሆኖ በማግኘቱ ከዛሬ ግንቦት 13 ቀን 2014 ዓ.ም ጀምሮ ተግባራዊ እንዲሆን ወስኗል፡፡

በመጨረሻ ምክር ቤቱ የተወያየው የትምህርትና ስልጠና ባለስልጣንን ስልጣን፣ ተግባር እና አደረጃጀት ለመወሰን በወጣው ረቂቅ ደንብ ላይ ነው፡፡ ለትምህርትና ስልጠና ባለስልጣን  የከፍተኛ ትምህርት አግባብነትና ጥራት ኤጀንሲ መብትና ግዴታዎች እንዲተላለፉ የተደረገ መሆኑን ተከትሎ ተቋሙ ስራውን በተሻለ ሁኔታ እንዲመራ የሚያስችል ረቂቅ ደንብ ተዘጋጅቶ ወይይት የተደረገበት ሲሆን በነጋሪት ጋዜጣ ታትሞ ከወጣበት ቀን ጀምሮ በስራ ላይ እንዲውል የሚኒስትሮች ምክር ቤት ወስኗል፡፡