በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ምክንያት ተቋርጦ የነበረው የማህፀን በር ካንሰር መከላከያ ክትባት ዛሬን ጨምሮ ለስድስት ተከታታይ ቀናት እንደሚሰጥ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ጤና ቢሮ አስታወቀ።
ቢሮው ጉዳዩን አስመልክቶ በሰጠው መግለጫ ክትባቱ በትምህርት ቤቶችና በጤና ጣቢያዎች ከዛሬ ጀምሮ ለተከታታይ ስድስት ቀናት እንደሚሰጥ አስታውቋል።
የቢሮው ኃላፊ ዶክተር ዮሐንስ ጫላ እንዳሉት፤ በኢትዮጵያ የማህፀን በር ካንሰር ከጡት ካንሰር ቀጥሎ በሁለተኛ ደረጃ ላይ የሚገኝ አስከፊ በሽታ ነው።
በኢትዮጵያ በየዓመቱ 7 ሺህ ሴቶች የማህፀን በር ካንሰር በሽታ የሚታይባቸው ሲሆን ከነዚህም 71 በመቶ የሚሆኑት ለሞት ይዳረጋሉ ነው ያሉት።
ሰማኒያ በመቶ በሚሆኑት ላይ ደግሞ በሽታው ከ10 እስከ 20 ዓመት ድረስ ምልክት ሳያሳይ ቆይቶ ድንገት እንደሚከሰት ተናግረዋል።
መከላከያ ክትባቱ ከ2011 ጀምሮ ዕድሜያቸው 14 ዓመት ለሆናቸው ልጃገረዶች በዓመት ሁለት ጊዜ ሲሰጥ ቢቆይም 2012 በተከሰተው የኮቪድ-19 ወረርሽኝ ምክንያት ተቋርጦ መቆየቱን ዶክተር ዮሐንስ አስታውሰዋል፡፡
በሽታውን ለመከላከል እየተሰጠ ከሚሰጠው ክትባት ጎን ለጎን ልጃገረዶች የስነ-ተዋልዶ ትምህርት እንዲያገኙና የቅድመ ካንሰር ሕክምናን ተደራሽ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑንም ጨምረው ገልጸዋል።
የክትባት መርሃ-ግብሩ በ2012 ዓ.ም የመጀመሪያ ዙር ክትባት ለወሰዱ 21ሺህ 809 ልጃገረዶች ሁለተኛ ዙር እንዲወስዱ እንደሚደረግ ኃላፊው መግለጹን ኢዜአ ዘግቧል፡፡