ነሐሴ30/2016(አዲስ ዋልታ) የምስራቅ ዕዝ የሀገራችንን ሰላም ሉአላዊነትና አንድነትን ለማስጠበቅ ከፍተኛ ዋጋ ከፍሏል ሲሉ ፊልድ ማርሻል ብርሀኑ ጁላ ገለጹ፡፡
የምስራቅ ዕዝ 47ኛ ዓመት የምስረታ በዓል “የምስራቁ ጮራ የኢትዮጵያ ወታደር ነን” በሚል መሪ ቃል በጅግጅጋ ከተማ እየተከበረ ይገኛል።
በበዓሉ ላይ ንግግር ያደረጉት የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሀኑ ጁላ የምስራቅ ዕዝ ተስፋፊውን የዚያድ ባሬ ጦር ጨምሮ የተለያዩ የሽብር ሀይሎችን በመከላከልና በተለያዩ የሀገራችን ክፍሎች የተሰጠውን ግዳጅ በጀግንነት የተወጣ ነው ብለዋል፡፡
ሠራዊቱ በቀጠናው ያለውን የተስፋፊዎች የጦርነት ነጋሪት ጉሸማ ለመመከት የሚያስችል የተሟላ ወታደራዊ ቁመና ላይ እንደሚገኝና ህዝቡ ላይ ስጋት ለመፍጠር የሚሞክሩ ተላላኪዎችን እንደማይታገስም ገልጸዋል፡፡
በምስራቁ የሀገሪቱ ቀጠና የጦርነት ነጋሪት የሚጎስሙ እነዚህ ተስፋፊ ኃይሎች የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት የሚያስከብር ጠንካራ መከላከያ መኖሩን መዘንጋት የለባቸውም ሲሉም አክለዋል።
የምስራቁ የሀገራችንን ድንበር ለመመከት ለዕዙ የሚያስፈልገውን ማንኛውንም ድጋፍ መከላከያ እንደሚያደርግ እና መላው የኢትዮጵያ እና የክልሉ ማህበረሰብ ለዕዙና ለሰራዊቱ የሚያደርጉትን ድጋፍ አጠናክረው እንዲቀጥሉ ጥሪ ማቅረባቸውን ከመከላከያ ሰራዊት ትስስር ገጽ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል።
የሶማሌ ክልል ርዕሰ መሥተዳደር ሙስጠፌ ሙሀመድ በበኩላቸው የሀገር መከላከያ ሠራዊት የተሰጠውን ተልዕኮ በብቃት በመፈፀም የሀገርና የህዝብ ኩራት መሆን የቻለ ታላቅ ሠራዊት ነው ብለዋል።
የሰሜኑን የሕግ ማስከበር ዘመቻ እንደ መልካም አጋጣሚ በመቁጠር፣ በምስራቁ የሀገሪቱ ክፍል ሰርጎ የገባውን የአልሻባብ ኃይል በመደምሰስ የአካባቢውን ሰላምና ደህንነት ማረጋገጥ መቻሉን አንስተዋል።
ሠራዊቱ ከሀገር አልፎ ዓለም አቀፋዊ ተልዕኮዎችን እየተወጣ የሚገኝ ሠራዊት ነው ሲሉም ተናግረዋል።