የምናርፈው ስንበለፅግ ብቻ ነው – ከንቲባ አዳነች አቤቤ

ጳጉሜ 2/2014 (ዋልታ) ከተባበርን፣ ከተደማመጥን እና ከተጋን አቅማችን ከዚህ በላይ ነውና የምናርፈው ስንበለፅግ ብቻ ነው ሲሉ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ ገለጹ።
ከንቲባ አዳነች በቂርቆስ ክፍለ ከተማ በጉምሩክ ኮሚሽን የተገነቡ 27 መኖርያ ቤትና 8 የንግድ ቤቶችን፤ በመከላከያ ኢንተርፕራይዝ የተገነቡ 8 ቤቶችን፤ እንዲሁም በሄኒከን ቢራ የተገነቡ 50 ቤቶችን በድምሩ 103 ቤቶችን ለአቅመ ደካሞች አስረክበዋል።
ከንቲባዋ የነዋሪዎችን ችግር መቅረፍ የሚችሉ ስራዎች በመስራታቸው ደስተኛ እንደሆኑ ገልፀው ስለወገኖቻቸው ህመም የሚያስቡ በጎ ፍቃደኞች ስለበዙ የቂርቆስን ጨምሮ ከ952 በላይ ቤቶችን አስረክበናል ብለዋል።
ይህ የሚያሳየው ከተባበርን ከተባበርን፣ ከተደማመጥን እና ከተጋን አቅማችን ከዚህ በላይ መሆኑን ነው ያሉት ከንቲባዋ አመራሮቻችንም ሆነ በጎ ፍቃደኞች በርቱልን የምናርፈው ስንበለፅግ ብቻ ነው ብለዋል፡፡
የክፍለ ከተማው ዋና ስራ አስፈፃሚ በበኩላቸው የከተማ አስተዳደሩ አንዱ ተግባር ቤቶችን ለህብረተሰቡ ገንብቶ ማስረከብ መሆኑን ገልፀው በዛሬው ሳናበቃ በቀጣይም የነዋሪዎቻችንን ምቾት ለመጠበቅ ጠንክረን እንሰራለን ማለታቸውን የከንቲባ ጽ/ቤት መረጃ አመላክቷል።