የምክር ቤቱ አመራሮች ለሰላም ስምምነቱ ተፈፃሚነት በትኩረት እንሰራለን አሉ

ኅዳር 8/2015 (ዋልታ) የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ምክር ቤት ምክትል ፕሬዝዳንት አህመድ ሁሴን በፕሪቶሪያ የተፈረመው የሰላም ስምምነት ተፈፃሚ እንዲሆን ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ባለድርሻ አካላትን በማሳተፍ የሰብዓዊ አገልግሎቶችን ተደራሽ ለማድረግ ብሎም በሰላም ግንባታ ላይ ለመስራት እቅድ ይዘው እየተንቀሳቀሱ እንደሚገኙም ነው ምክትል ፕሬዝዳንቱ የተናገሩት፡፡

ስምምነቱ ተፈፃሚ እንዲሆን ለማስቻል ሁለቱ ወገኖች የገቧቸውን ቃሎች እንዲያከብሩ ትኩረት ሰጥተው እንደሚሰሩ የገለፁት ደግሞ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ምክር ቤት ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባል ፅጌሬዳ ዘውዱ ናቸው፡፡

ስምምነቱ አፍሪካዊ ችግሮችን በአፍሪካዊያን መፍታት እንደሚቻል ያሳየና ለሌሎች አገራትም ተምሳሌት መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ስምምነቱ በቅርቡ ለሚካሄደው ሀገራዊ የምክክር መድረክ ምቹ መደላድል የሚፈጥር ከመሆኑ ባሻገር የበለፀገች ኢትዮጵያን ለመፍጠር የሚደረገው ጥረት እውን የሚሆነው በሰላም ብቻ መሆኑን ያሳየ እንደሆነም አመራሮቹ ገልፀዋል።

የሰላም ስምምነቱ የተሳካ እንዲሆን ሁሉም ባለድርሻ አካላት ኃላፊነታቸውን ሊወጡ እንደሚገባ የሲቪል ማህበረሰብ ድርጅቶች ምክር ቤት ጥሪ አቅርቧል፡፡

በሱራፌል መንግስቴ