የረመዳን ጾምን ምክንያት በማድረግ 600 ለሚጠጉ አባዎራዎች የማዕድ ማጋራት ድጋፍ ተደረገ

መጋቢት 25/2014 (ዋልታ) በአዲስ አበባ ከተማ የአደሬ ሰፈር የልማትና መረዳጃ ማኅበር የረመዳን ጾምን ምክንያት በማድረግ 600 ለሚጠጉ አባዎራዎች የማዕድ ማጋራት ድጋፍ አድርጓል፡፡
በድጋፉ ወቅት የማኅበሩ ሰብሳቢ ኑረዲን ረሺድ ማኅበሩ የማዕድ ማጋራት ድጋፉን ያደረገው በተለያዩ የዓለም ሀገራት ከሚኖሩ የአካባቢው ተወላጆችና ከአባላቱ ባሰባሰበው 780 ሺሕ ብር መሆኑን ገልጸዋል፡፡
በዚህም ማኅበሩ በተለምዶ “አደሬ ሰፈር” ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ለሚኖሩ አቅመ ደካማ ዜጎች ለአንድ አባዎራ 1 ሺሕ 300 ብር የሚያወጣ ሁለት ኪሎ ቴምር፣ አስር ኪሎ ዱቄት፣ አምስት ኪሎ ገብስና አምስት ኪሎ ሩዝ መሆኑንም አብራርተዋል፡፡
የአዲስ አበባ እስልምና ጉዳዮች ጽሕፈት ቤት ዋና ፀሐፊ ሼህ ሀሚድ ሙሳ በበኩላቸው ማንኛውም ማኀበረሰብ ከተባበረ፣ ከተቻቻለና ከተረዳዳ የሚያጋጥሙ ችግሮችን መፍታት ይቻላል ብለዋል፡፡
ጽሕፈት ቤቱ ማኅበሩ ለጀመረው በጎ ተግባር የሚጠበቅበትን ድጋፍ እንደሚያደርግም ማረጋገጣቸውን ኢዜአ ዘግቧል፡፡
ኢትዮጵያዊያን ከየትኛውም ጊዜ በላይ እርስ በርስ በመደጋገፍ በጋራ የሚቆሙበት ጊዜ ላይ መሆናቸውን የገለጹት ደግሞ የአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ ዋና ሥራ አስፈጻሚ ሽታዬ መሀመድ ናቸው፡፡
አገራችን ከጦርነት ማግስት ላይ በመሆኗ በርካታ ተፈናቃዮች እንዳሉ ገልጸው ይህን ችግር በአብሮነትና በወንድማማችነት መንፈስ መወጣት እንደሚገባም አመልክተዋል።
ለፈጣን መረጃዎች፦
ቴሌግራም https://t.me/WALTATVEth
አብራችሁን ስለሆናችሁ እናመሰግናለን!