የሰሜን ኮሪያ ጠ/ሚ ኪም ቶክ ሁን ለጠ/ሚ ዐቢይ የእንኳን ደስ አለዎት መልዕክት ላኩ

1
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ / ጠቅላይ ሚኒስትር ኪም ቶክ ሁን

ጥቅምት 5/2014 (ዋልታ) ኢትዮጵያ መስከረም 24 ቀን 2014 ዓ.ም አዲስ ምዕራፍ የጀመረችበትን አዲስ መንግስት መመስረቷን እንዲሁም ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በድጋሚ ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነው መመረጣቸውን ተከትሎ በርካታ ሀገራት የእንኳን ደስ አለዎት መልዕክት እያስተላለፉ ይገኛሉ፡፡

ከእነዚህ ሀገራት መካከል ሰሜን ኮሪያ አንዷ ሆናለች፡፡ የሰሜን ኮሪያ ጠቅላይ ሚኒስትር ኪም ቶክ ሁን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ በድጋሚ የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነው በመመረጥዎ እንኳን ደስ አለዎት ብለዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ አክለውም በስልጣን ዘመንዎ ለሀገርዎ ልማት፣ ብልጽግና እና ሰላም እንዲመጣ በሚያደርጉት ጥረት ሁሉ ስኬትን እመኝሎታለሁ ካሉ በኋላ፤ በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለው የሁለትዮሽ ግንኙነት፣ ወዳጅነት እና በትብብር የመስራት ፍላጎት እናጠናክራለን ብለዋል፡፡

በተመሳሳይ የሀገሪቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሪ ሰን ግዎን በበኩላቸው፣ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንንም እንዲሁ በድጋሚ በመመረጥዎ የእንኳን ደስ አለዎት መልካም ምኞት መልዕክት አስተላልፈዋል ሲል ኢዜአ ዘግቧል፡፡

የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ አክለውም “በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለው መልካም ግንኙነት እና ትብብር በቀጣይ በተጠናከረ መልኩ እናስቀጥላለን” ካሉ በኋላ በስራዎት ሁሉ ስኬትን እመኛለሁ ብለዋል፡፡

ኢትዮጵያ በአዲስ ምዕራፍ ጅማሮ አዲስ መንግስት ካዋቀረች በኋላ ቻይና፣ ሩሲያ፣ ቱርክ፣ ቬትናም፣ ኳታር፣ ደቡብ ኮሪያ እና በርካታ የአፍሪካ ሀገራት መሪዎች የመልካም ምኞት መልዕክት ማስተላለፋቸውን አስታውሷል፡፡