የሲዳማ ክልል በ9 ወራት 3 ነጥብ 9 ቢሊዮን ብር ገቢ ሰበሰበ

መጋቢት 25/2014 (ዋልታ) የሲዳማ ክልል በዘጠኝ ወራት ጊዜ ውስጥ 3 ነጥብ 9 ቢሊዮን ብር ግብር መሰብሰቡን አስታወቀ።
ክልሉ በ2013 በጀት ዓመት ግምባር ቀደም ለሆኑ 21 ግብር ከፋዮች የዕውቅና፣ የምስጋና ምስክር ወረቀትና ዋንጫ አበርክቷል።
በመድረኩ የተገኙት የክልሉ ርዕሠ መስተዳድር ደስታ ሌዳሞ ግብርን በተገቢው በመሰብሰብ ለሕዝብ የልማትና መልካም አስተዳደር ጥያቄዎች ምላሽ መስጠት እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
የክልሉ ገቢዎች ባለስልጣን ኃላፊ ኃይሉ ጉዱራ በ2014 በጀት ዓመት 5 ነጥብ 5 ቢሊዮን ብር ለመሰብሰብ ያቀደው የሲዳማ ክልል ባለፉት ዘጠኝ ወራት ከ3 ነጥብ 9 ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ በመሰብሰብ ከዕቅዱ በላይ ማከናወን እንደቻለ ተናግረዋል።
ገቢው ካለፈው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነጻጸር የ1 ነጥብ 2 ቢሊዮን ብር ብልጫ አለው ያሉት ኃላፊው የተሰበሰበው ገንዘብ ካለው የመልማት ፍላጎትና የገቢ አቅም አንጻር በቂ እንዳልሆነ ጠቅሰዋል።
በመሆኑም ገቢውን በተገቢው መንገድ ለመሰብሰብና ለማሳደግ ይሰራል ማለታቸውን ኢዜአ አስነብቧል።
በበጀት ዓመቱ 34 ነጥብ 8 ሚሊየን ብር በመክፈል ግንባር ቀደም የሆነው የኢታብ ሳሙና ፋብሪካ ማኔጅንግ ዳይሬክተር መምህር ተስፋዬ አበበ ሽልማቱ የበለጠ ለመስራት አቅም ይፈጥራል ብለዋል።
ድርጅታቸው በተከታታይ ዓመታት የሚጠበቅበትን ግብር በአግባቡና በወቅቱ በመክፈል የግሪን ካርድ ተሸላሚ መሆኑን ተናግረዋል።