የሲዳማ ክልል የቱሪዝም ቀንን አከበረ

ጥቅምት 11/2015 (ዋልታ) የሲዳማ ክልል የቱሪዝም ቀንን በተለያዩ መርኃግብሮች አክብሯል፡፡

ክልሉ ያሉት የሚዳሰሱ እና የማይዳሰሱ ቅርሶች የቱሪዝም ዘርፉን ከማሳደግ ባሻገር ለገፅታ ግንባታ ከፍተኛ አስተዋጽዖን እያበረከቱ እንደሚገኝ ተገልጿል::

የክልሉን የቱሪዝም ሀብት በማልማት የገቢ ምንጭ ለማድረግ እየተሰራ መሆኑን  የገለፁት የሲዳማ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ደስታ ሌዳሞ በዚህም መሰረት ክልሉ ካሉት የቱሪዝም መዳረሻዎች መካከል አንዱ የሆነውን የጋራ አምባ ተራራ ወደ ፓርክነት የማሳደግ ስራ መሰራቱን ጠቁመዋል::

ሀገር ከቱሪዝም ዘርፉ የምታገኘውን ገቢ ለማሳደግ በየአካባቢው ያሉ የተፈጥሮ ገፀ በረከቶችን ለቱሪዝም አመቺ በማድረግ የመሰረተ ልማት ግንባታዎችንና መሰል ልማቶች ላይ ትኩረት ሰጥቶ መስራት ይገባልም ብለዋል::

በአካባቢው የሚገኙትን የቱርስት መዳረሻዎች በማልማት እና ምቹ ከባቢን በመፍጠር ክልሉ ከቱሪዝም ዘርፍ የሚያገኘውን ገቢ ለማሳደግ እንደሚሰራ የገለጹት ደግሞ የክልሉ ባህል ቱሪዝምና ስፖርት ቢሮ ኃላፊ ጀጉ አገኘሁ ናቸው::

 

ሔብሮን ዋልታው (ከሀዋሳ)