የሶማሊያው ፕሬዝዳንት የሥልጣን ዘመናቸውን የሚያራዝመውን ውሳኔ በመተው ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ እንዲካሄድ ጥሪ አደረጉ

የሶማሊያው ፕሬዝዳንት ሞሐመድ አብዱላሂ ፋርማጆ
ሚያዝያ 20/2013 (ዋልታ) – የሶማሊያው ፕሬዝዳንት ሞሐመድ አብዱላሂ ፋርማጆ የሥልጣን ዘመናቸውን በሁለት ዓመት ለማራዘም እያደረጉት የነበረውን ሙከራ በመተው ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ እንዲካሄድ ጥሪ አደረጉ።
ፕሬዝዳንት ፋርማጆ በመገናኛ ብዙኃን አማካይነት ለአገሪቱ ሕዝብ ባስተላለፉት መልእክት አዲስ ፕሬዝዳንታዊ ምርጫ እንዲካሄድ ጥሪ አድርገዋል።
የሥልጣን ጊዜያቸው ካበቃበት ከየካቲት ወር ጀምሮ ሲቃወሟቸው የነበሩት ጠቅላይ ሚኒስትራቸው ውዝግቡ ከተጀመረ በኋላ ላደረጉት አዎንታዊ ጥረትም አመስግነዋቸዋል።
ፕሬዝዳንት ፋርማጆ በመጪው ቅዳሜ በአገሪቱ ፓርላማ ቀርበው ሊካሄድ ታቅዶ በነበረው ምርጫ ዙሪያ ባለፈው መስከረም የተደረሰውን ስምምነት ወደነበረበት እንዲመለስ ያደርጋሉ ተብሎ ይጠበቃል።
በዚህም ከሳምንታት በፊት የምክር ቤት አባላት የፕሬዝዳንቱ የሥልጣን ዘመን ለሁለት ዓመት እንዲራዘም ያስተላለፈው ውሳኔ የሚሻር ይሆናል ነው የተባለው።
ባለፈው የፈረንጆች ዓመት በተደረሰው ስምምነት የአገሪቱ ጎሳ መሪዎች ተወካዮቻቸውን ከመረጡ በኋላ እነሱም በበኩላቸው፣ የአገሪቱን ፕሬዝዳንት የሚመርጡ የፌደራሉ የምክር ቤት አባላትን ይሰይማሉ።
ፕሬዝዳንቱ “ከዚህ በፊት እንዳደረኩት አሁንም በሶማሊያ ውስጥ በወቅቱና ሠላማዊ በሆነ መንገድ ምርጫ እንዲደረግ ያለኝን ፍላጎት በድጋሚ ላረጋግጥ እወዳለሁ” ብለዋል።
የአገሪቱ የጸጥታ ተቋማት የሠላማዊ ሰዎችን ደኅንነት ለማስጠበቅ በሚያደርጉት ጥረት ውስጥ “የአገሪቱን መረጋጋት ከሚያውክ ድርጊቶች” እንዲቆጠቡ ጥሪ አቅርበዋል።
የፕሬዝዳንቱን የሥልጣን ዘመን መራዘም ተከትሎ በሞቃዲሾ ውስጥ ባሉ ታጣቂዎች መካከል ባለፈው ሳምንት ማብቂያ ላይ የተፈጠረውን ግጭት በመሸሽ ነዋሪዎች ወደ ሌሎች አካባቢዎች እየሄዱ መሆናቸው ተገልጿል።
በተጨማሪም የተከሰተው አለመረጋጋት ታጣቂው እስላማዊ ቡድን አል ሻባብ ሊጠቀምበት ይችላል የሚል ስጋት መፍጠሩን ቢቢሲ ዘግቧል።