የሶማሌ ክልል አዲስ የመንግሥት ምስረታ ሰኞ ይካሄዳል

ጥቅምት 6/2014 (ዋልታ) የሶማሌ ክልል ምክር ቤት ስድስተኛ ዓመት አንደኛ መደበኛ ስብሰባ እና የመንግሥት ምስረታ ሰኞ ጥቅምት 8 ይካሄዳል፡፡
የክልሉ ምክር ቤት በ6ኛው አገራዊ ምርጫ ለክልል ምክር ቤት አሸናፊ ለሆኑ አዳዲስ የምክር ቤት አባላት በዛሬው ዕለት ስልጠና እየሰጠ ነው፡፡
ስልጠናው በምክር ቤቱ ስነ ምግባርና ሕግ፣ በአባላት መብትና ግዴታ እንዲሁም ስለ ምክር ቤቱ የሥራ አደረጃጀት እና አጠቃላይ መሰረታዊ መርሆች ላይ ያተኮረ መሆኑ ተገልጿል፡፡
የሶማሌ ብልጽግና ፓርቲ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ መሐመድ ሻሌ 90 በመቶ አዲስ የሚሆኑት የምክር ቤት አባላት ሰኞ አዲሱን ክልላዊ መንግሥት ያዋቅራሉ ማለታቸውን ከክልሉ መገናኛ ብዙኃን ኤጀንሲ ያገኘነው መረጃ ያሳያል፡፡