የሶማሌ ክልል የሀይማኖት መሪዎች የአሸባሪው አልሸባብን ታጣቂ ቡድን ድርጊትና አስተሳሰብ አወገዙ

ሐምሌ 27/2014 (ዋልታ) የሶማሌ ክልል የሀይማኖት መሪዎች በወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ የሶማሌ ክልል ፕሬዝዳንት ሙስጠፋ ሙሁመድ በክብር እንግድነት በተገኙበት ባካሄዱት ውይይት በአሸባሪው የአልሸባብ ታጣቂ ቡድን በሀገራችን ላይ በተለይ በክልሉ የተቃጣውን ጥቃት፣ ድርጊትና አስተሳሰብ አወገዙ።

ከክልሉ ሁሉም አከባቢዎች የተወጣጡ የሀይማኖት መሪዎች ትላንት በጅግጅጋ ከተማ በወቅታዊ ክልላዊና ሀገራዊ ጉደዮች ዙሪያ ሰፊ ውይይት ያካሄዱ ሲሆን፣ ከውይይቱ በኋላም ባለ ዘጠኝ ነጥብ የአቋም መግለጫ በማውጣት ውይይቱን አጠናቀዋል።
ርዕሰ መስተዳድር ሙስጠፌ ከውይይቱ በኋላ በማህበራዊ የትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት ጽሁፍ እንደገለጹት፤ የሀይማኖት አባቶቹ የሚደነቅ መሆኑን ገልጸው በተለይ አልሸባብን መዋጋት ሀይማኖታዊ ግዴታ መሆኑን መግለጻቸው አግባብነት ያለው ነው ብለዋል፡፡

ከክልሉ የመንግስት ኮሙዩኒኬሽን የተገኘው የሀይማት አባቶቹ ያወጡት የአቋም መግለጫ እንደሚከተለው ነው ቀርቧል፡-
እኛ የሶማሌ ክልል የሀይማኖት መሪዎች በቅርቡ አሸባሪው የአልሸባብ ቡድን በክልላችንና በሀገራችን ላይ የተቃጣውን ወረራ አስመልክቶ የሚከተለውን ባለ ዘጠኝ ነጥብ የአቋም መግለጫ አውጥተናል፡፡
• በቅርቡ አሸባሪዎች በክልሉ ያደረጉት ወረራና የትንኮሳ ድርጊት እናወግዛለን።
• የክልሉ የፀጥታ ሀይሎችና መላው የሀገራችን ሠራዊት በአሸባሪው አልሸባብ ላይ በወሰዱትን እርምጃና ዘመቻ፣ ለተመዘገበው ታሪካዊ ድል ድጋፋችን እና አድናቆታችንን እንገልፃለን።
• አሸባሪውን አልሸባብ ለመደምሰስ የክልሉ መንግስት የወሰደው አስደናቂ ተግባር እና የክልሉ ህዝብ ለልዩ ሃይልና ለሀገር መከላከያ ሰራዊት ያደርገውን ድጋፍ እናደንቃለን።
• ህብረተሰቡ በአጠቃላይ ለሰራዊቱ የሚያደርገውን ድጋፍ እንዲያጠናክር እንጠይቃለን።
• ህብረተሰቡ የአልሸባብ ሽብርተኛ ቡድን የተሸከሙትን የተዛቡ አመለካከቶች፣ ድርጊቶች እና የተሳሳቱ አስተሳሰቦች እንዳይታለሉና እንዲጠነቀቁ እንጠይቃለን።
• አልሸባብ በእስልምና ሃይማኖት ውስጥ ምንም አይነት መሰረት የሌለው አሸባሪ ቡድን መሆኑን ለማህበረሰቡ እንገልፃለን።
• አሸባሪው የአልሸባብ ቡድን የሚያምኑትና የሚያራምዱት የተሳሳቱ አስተሳሰቦች ወይም አይዲዮሎጂ፣ በየደረጃው ያለው የክልሉ ሊቃውንትና የሀይማኖት መሪዎች ለህብረተሰቡ በየጊዜው እንዲያስረዱና የሽብርተኛ ቡዱኑ ፍላጎት የሰውን ደም ማፍሰስ እንደሆነ ለህዝቡ እንዲናገሩ እናሳስባለን።
• የአሸባሪውን አልሸባብ መጥፎና የተሳሳተ አስተሳሰብ ህዝብ በሚሰበሰብባቸው ቦታዎች እና በእምነት ተቋማት ውስጥ ለህዝቡ ማሳወቅና ግንዛቤ እንዲሰጥ እናሳስባለን።
• 9.ህዝቡ ለደህንነትና ለፀጥታ አካላት ትዕዛዝ እንደ ከዚህ ቀደሙ ሁሉ በመታዘዝ እና በመተባበር ለሰላም መጠናከር ህዝቡ የበኩሉን ሚና እንዲወጣ ጥሪ እናቀርባለን።