የሶማሌ የሀገር ሽማግሌዎች ሰላምን ለማጠናከር ከመንግሥት ጎን ሆነን እንሰራለን አሉ

ግንቦት 9/2014 (ዋልታ) ለሰላም፣ ፀጥታ መጠናከርና ህገ-ወጥ ተግባራትን ለመታገል ከመንግሥት ጎን ሆነው እንደሚሰሩ የሶማሌ ክልል የሀገር ሽማግሌዎች ገለጹ፡፡

የሶማሌ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ሙስጠፌ ሙሀመድ በዛሬው ዕለት ከክልሉ የሀገር ሽማግሌዎች ጋር ተወያይተዋል።

በክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ሙስጠፌ ሙሀመድ እና በሶማሌ ብልፅግና ፓርቲ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ መሐመድ ሻሌ የተመራ የሀገር ሽማግሌዎች በጋራ የተደረገው ምክክር መድረክ በከተማና በድንበር አካባቢ ያለው ሰላምና ፀጥታ ሁኔታ፣ እየናረ የመጣው የዋጋ ግሽበትን መቆጣጠር የሚቻልበት መንገድ፣ የነዳጅ እጥረትና ተያያዥ ችግሮች እና የፍትህ አገልግሎት አሰጣጥን የበለጠ ማጠናከርን አላማው ያደረገ ነው ተብሏል።

ተሳታፊ የሀገር ሽማግሌዎችም መንግሥት በሰላምና ፀጥታ ማስፈን ላይ ከከተሞች አንስቶ እስከ ድንበር ድረስ እየሰራ ያለው ትልቅ ሥራ የሚበረታታና ሁሉም የፀጥታ አካል በያለበት መስክ አጠናክሮ እንዲቀጥል ጠይቀዋል።

በተለይም ከከተሞች ዕድገት እና መስፋት ጋር ተያይዞ መንግሥት በከተሞች አካባቢ ያለውን የፀጥታ ተቋማትን የበለጠ ማስፋትና ማጠናከር እንደሚገባ የሀገር ሽማግሌዎች ተናግረዋል።

በሌላ በኩል ከዕለት እለት እየናረ የመጣው የዋጋ ግሽበትን በተመለከተ ከቀረጥ ነፃ የተፈቀዱ የምግብ ሬሽኖችን በስፋት እንዲገቡ መፍቀድና አሁን ካለው የገበያ ሥርዓት በተጨማሪ ተወዳዳሪ የሚሆኑ ምርቶችን በስፋትና በመጠን የሚያቀርቡ አስመጪዎችን ማብዛት እንደሚገባና ሰው ሰራሽ የገበያ እጥረትና ገበያው እንዳይረጋጋ የሚያደርጉ አካላትን ተከታትሎ ለህግ ማቅረብና እርምጃ መውሰድ እንደሚገባም ነው የተገለጸው።

እንደመፍትሄ የክልሉ መንግሥት አሁን ላይ ዕቅድ ይዞ የጀመረው የራስን የምግብ ዋስትና ለማረጋገጥ  በሁሉም የክልሉ ዞኖች  የግብርና እርሻ ሥራ ዋና መፍትሔ በመሆኑ ክልሉ ባሉት ወንዞች ላይም ሆነ በተገኘው ዝናብ ተጠቅሞ ሕዝቡ ግብርናው ላይ ጠንክሮ መስራት ይገባል ብለዋል፡፡

አያይዘውም በክልሉ እየተስተዋለ የመጣውን የነዳጅ እጥረት መንግስት ችግሩን ለይቶ በማጥናት አፋጣኝ መፍትሔ ሊፈልግለት እንደሚገባም አመላክተዋል።

ርዕሰ መስተዳድር ሙስጠፌ ሙሀመድ በበኩላቸው ለተሰጡት የተለያዩ ሃሳብና አስተያየቶችን ጠቃሚና ጊዜውን የጠበቁ መሆናቸውን አንስተው  መንግሥት በተነሱት ሐሳቦች ላይ ትኩረት ሰጥቶ እንደሚሰራ ገልጸዋል፡፡

የሀገር ሽማግሌዎችም በሰላምና ፀጥታውም ሆነ ህገ-ወጥ አሰራርን በማስረፅ በዜጎች ላይ አግባብ ያልሆነ አሰራርንና ፍትሐዊ ያልሆነ ተግባርን ከመንግሥት ጎን በመሆን ሊታገሉ እንደሚገባ መግለጻቸውን ከክልሉ መገናኛ ብዙኃን ያገኘነው መረጃ አመላክቷል።