የበይነ መረብ የንግድ ምዝገባና ፈቃድ አገልግሎትን ለማሻሸል ዝግጅት እየተደረገ ነው

ታኅሣሥ 18/2019 (ዋልታ) የበይነ መረብ የንግድ ምዝገባና ፈቃድ አገልግሎት አሰጣጥ ሂደቱን ተደራሽነት፣ ፍጥነትና የተገልጋዩን የግልጋሎት ቅልጥፍና ለማሻሻል በኢንተርኔት ካፌ የንግድ ሥራ መደብ ተሰማርተው ከሚሰሩ የንግድ ተቋማት ጋር አብሮ ለመስራት ዝግጅት ማድረጉን የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡

አገልግሎት አሰጣጡን የተሻለ በማድረግ ደንበኞች በማንኛውም ቦታ አገልግሎቱን ማግኘት እንዲችሉ አማራጮችን ማስፋት አስፈላጊ መሆኑን በሚኒስቴሩ የኢንፎርሜሽንና ኮሙዩኒኬሽን ቴክኖሎጂ ዳይሬክተሩ ፀጋው በለጠ ተናግረዋል፡፡

አገልግሎቱ የተጠቃሚዎችን ጊዜና ገንዘብ በመቆጠብና እንግልትን በማስቀረት ረገድ የሚጫወተው ሚና ከፍተኛ ቢሆንም እንደ ሀገር ከ2 ነጥብ 1 ሚሊየን በላይ በንግድ ስራ ከተሰማሩ የዘርፉ ተገልጋዮች ውስጥ ከአንድ በመቶ የማይበልጡት የአገልግሎቱ ተጠቃሚ መሆናቸውን ጠቅሰዋል፡፡

ለተጠቃሚዎች የተሻለ አማራጭና የአገልግሎት ተደራሽነትን በማስፋት ለንግዱ ማኅበረሰብ  ጊዜንና ገንዘብን ቆጣቢና ተደራሽ የሆነ አገልግሎት ለመስጠት እየተሰራ መሆኑን ከንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ አመላክቷል፡፡

በሚኒስቴሩ የዘርፉ አማካሪ ግዛው ተክሌ በበኩላቸው የበየነመረብ ንግድ ምዝገባና ፈቃድ አገልግሎቱን ሁሉን ዐቀፍና ተደራሽ ለማድረግ ከኢንተርኔት ካፌ ባለቤቶች ጋር አብሮ መስራት ወሳኝ ነው ብለዋል፡፡

ከጥቂት ቀናት በኋላ ሥርዓቱ የሚመራበት ህጋዊና ተቀባይነት ያለው የስራ ውል የሚያስፈልግ በመሆኑ የተዘጋጀው የውል ሰነድ በህግ ባለሙያዎች አስተያየት ከተሰጠበት በኋላ የኢንተርኔት ካፌ ባለቤቶች የበየነመረብ የንግድ ምዝገባና ፈቃድ አገልግሎት እንዲሰጡ የሚያስችል የመግባቢያ ሰነድ ከሚኒስቴሩ ጋር በመፈራረም ወደ ስራ ይገባል ተብሏል፡፡