የበጎ ፈቃድ የማህበረሰብ አገልግሎት ፕሮግራምን በጋራ ለማስፈፀም የመግባቢያ ሰነድ ስምምነት ፊርማ ተካሄደ

የሰላም ሚኒስቴር ብሔራዊ የበጎ ፈቃድ የማህበረሰብ አገልግሎት ፕሮግራምን በጋራ ለማስፈፀም ከክልሎችና ከከተማ አስተዳደር ሰላምና ፀጥታ ቢሮዎችና ከዩኒቨርስቲዎች ጋር የመግባቢያ ሰነድ ስምምነት ፊርማ ስነ ስርዓት ተካሂዷል።

በፊርማ ስነ ስርዓቱ ላይ የሰላም ሚኒስትር ወ/ሮ ሙፈሪሃት ካሚል ብሔራዊ የበጎ ፈቃድ የማህበረሰብ አገልግሎት ፕሮግራም ወጣቶች መሰረታዊ የሆኑ የሰላም እሴቶችን አዉቀዉ ወደ ተግባር እንዲያዉሉ ታስቦ የተቀረፀ ፕሮግራም ነዉ ብለዋል።

ሚኒስትሯ አክለዉም ፕሮግራሙ ኢትዮጵያ አገራቸውን የሚወዱና የአገልጋይነት ስሜት የተላበሱ ወጣቶችን ለማፍራት ያለመ ነዉ ብለዋል።

የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስትር ዶ/ር ሳሙኤል ኡርካቶ በበኩላቸዉ ኢትዮጵያ የወጣቶች ሀገር መሆኗን ገልፀዉ ይህ ፕሮግራም ወጣቶች በትምህርት ያገኙትን እዉቀት ወደ ተግባር ለመቀየር ትልቅ ፋይዳ አለዉ ብለዋል።

ዶ/ር ሳሙኤል የሰላም ሚኒስቴር ይህን ሀላፊነት ወስዶ በመንቀሳቀሱ አመሰግነዉ የሳይንስና ከፍተኛ ትምህርት ሚኒስቴር በጎ ፈቃደኛ ወጣቶችን ለማገዝ ዝግጁ ነዉ ብለዋል።

የበጎ ፈቃድ የማህበረሰብ አገልግሎት ፕሮግራም ሁለት ዙር ያለዉ ሲሆን በመጀመሪያው ዙር ከከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የተመረቁ ወጣቶችን የሚያካት ሲሆን በሁለተኛዉ ዙር ደግሞ ከቴክኒክና ሙያ ተቋማት የተመረቁ ወጣቶችንና ትምህርት ያቋረጡ ወጣቶችን ያካትታል ተብሏል::
(ምንጭ፡- የሰላም ሚኒስቴር )