የባሕር ዳር ከተማ በኅልውና ዘመቻው ለተሰው ቤተሰቦች የመኖሪያ ቤትና የመስሪያ ሱቅ እንዲሰጣቸው ወሰነ

ጥር 16/2014 (ዋልታ) የባሕር ዳር ከተማ አስተዳደር የአገራቸውንና የሕዝባቸውን ሉኣላዊነት ለማስጠበቅ ሲሉ በኅልውና ዘመቻው በግንባር ተሰልፈው ለተሰው ጀግኖች ቤተሰቦች የመኖሪያ ቤትና የመስሪያ ሱቅ ቅድሚያ እንዲሰጣቸው መወሰኑን አስታወቀ።
የአስተዳደሩ ኮሙዩኒኬሽን መምሪያ ኃላፊ በትግሉ ተስፋሁን ለኢዜአ እንደገለጹት አገርን ለማፍረስ አቅዶ የተነሳውን አሸባሪው የትሕነግ ቡድን ለመደምሰስ በርካታ የፀጥታ አካላት ከባሕር ዳር ከተማ ወደ ግንባር ዘምተዋል።
የከተማ አስተዳደሩ ከንቲባ ኮሚቴ ለሕዝባቸውና ለአገራቸው ሲሉ አሸባሪውን ቡድን ሲፋለሙ መስዋዕትነት ለከፈሉ ጀግኖች የቀበሌ የመኖሪያ ቤት ቅድሚያ እንዲሰጣቸው መወሰኑን ገልፀዋል።
በተጨማሪም በተለምዶ “ጋጃ መስክ” ተብሎ በሚጠራው አካባቢ ከተመሰረተው የገበያ ቦታ የመስሪያ ሱቅ ቅድሚያ እንዲሰጣቸው መወሰኑን ተናግረዋል።
“ከተማ አስተዳደሩ በጀግንነት ለተሰው ቤተሰቦች የሚያደርገው ድጋፍ ጀግኖቹ የከፈሉትን ዋጋ ይተካል በሚል ሳይሆን ከቤተሰቦቻቸው ጎን አለን ለማለት ነው” ብለዋል።