የብልጽግና ፓርቲ ዋናው ጽሕፈት ቤት ለአቅመ ደካሞች ያስገነባቸውን ቤቶች አስረከበ

ጳጉሜ 1/2014 (ዋልታ) የብልጽግና ፓርቲ ዋናው ጽሕፈት ቤት በአራዳ ክፍለ ከተማ ወረዳ 6 ልዩ ስሙ ሰባ ደረጃ ተብሎ በሚጠራው አከባቢ ለአቅመ ደካሞችና በአነስተኛ ገቢ ለሚተዳደሩ ዜጎች ያስገነባቸውን ቤቶች ዛሬ አስረክቧል።
የበጎነት ቀንን በማስመልከት ቤቶቹን ያስረከቡት በብልጽግና ፓርቲ የፖለቲካና ርዕዮተ ዓለም ዘርፍ ሃላፊ አብርሀም አለኸኝ እና ሌሎች ከፍተኛ የፓርቲው አመራሮች ናቸው፡፡
የፓርቲ ጽሕፈት ቤቱ ከ5 ሚሊየን ብር በላይ ወጪ በማድረግ ለ11 አባወራዎች ቤቶችን ደረጃቸውን በጠበቀ መልኩ ማስገንባቱ ተነግሯል።
ቤት የተረከቡ ነዋሪዎች በሰጡት አስተያየትም ከዚህ ቀደም በአስቸጋሪ የኑሮ ሁኔታ ውስጥ እንደነበሩ ጠቅሰው፤ አሁን ደረጃውን የጠበቀ ቤት በመረከባቸው ደስታ እንደተሰማቸው ገልጸዋል፡፡
የበጎነት ቀን ዛሬ ጳጉሜ 1/2014 ዓ.ም በመላው ኢትዮጵያ በጎ ተግባራትን በመፈጸም ታስቦ መዋሉን የፓርቲው መረጃ አመላክቷል።