የብልጽግና ፓርቲ የሥራ ኃላፊዎች የልማት ሥራዎችን እየጎበኙ ነው

ግንቦት 14/2014 (ዋልታ) በቡታጅራ ማዕከል ሲሰለጥኑ የነበሩት የብልጽግና ፓርቲ የሥራ ኃላፊዎች በጉራጌ ዞን መስቃን ወረዳ በሞዴል አርሶ አደሮች እየለማ ያለውን የአትክልትና ፍራፍሬ ልማት ሥራዎችን እየጎበኙ ነው።
የዞኑ አርሶ አደሮች በተለይ አቮካዶ በልማት ወደ ውጭ ኤክስፖርት እያደረገ መሆኑም በጉብኝቱ ወቅት ተጠቁሟል።
የደቡብ ብልጽግና ፓርቲ ጽ/ቤት ኃላፊ ጥላሁን ከበደ እንደገለጹት በክልሉ በተለያዩ አካባቢዎች እየለማ ያለው የአትክልትና ፍራፍሬ ሥራ በአጭር ጊዜ ከድህነት ለመውጣት የምናደርገውን ጥረት ያግዛል ብለዋል።
እንደ ኃላፊው ገለጻ በሞዴል አርሶ አደሮች እየተካሔደ ያለው የግብርና ስራ የውጭ ምንዛሬን ከማስገኘት ባለፈ ለበርካታ ወጣቶች የስራ እድል መፍጠር ያስችላል።
በየደረጃው እየተካሄደ ያለው የአትክልትና ፍራፍሬ ልማት ስራ ይበልጥ ተጠናክሮ መቀጠል አለበት ብለዋል።
በጉብኝቱ የተሳተፉ አመራሮች በክልሉ በልዩ ልዩ የግብርና ልማት ሥራ የተሰማሩ የኅብረተሰብ ክፍሎች እያካሄዱት ያለው የልማት ሥራ ሀገሪቱ ያጋጠማትን የኢኮኖሚ ጫና ለመቋቋም ያግዛል ብለዋል።
በሞዴል አርሶ አደሮች የተጀመረው ልማት ወደ ሁሉም የኅብረተሰብ ክፍል እንዲዳረስ መስራት ይገባልም ብለዋል።
በክልሉ በአራት ማዕከላት ሰሞኑን በስልጠና ላይ የነበሩ የብልጽግና ፓርቲ የሥራ ኃላፊዎች በቡታጅራ፣በሆናዕና፣በአርባ ምንጭ ፣በወላይታ ሶዶ ከተማና አጎራባች ዞኖች በሞዴል አርሶ አደሮች የተከናወኑ የልማት ሥራዎችን ተሞክሮ እየተመለከቱ ነው።