የቦሌ ክፍለ ከተማ ከ400 ሚሊየን ብር በላይ ወጪ ያስገነባቸውን የተለያዩ ፕሮጀክቶች አስመረቀ

ነሐሴ 11/2014 (ዋልታ) የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ቦሌ ክፍለ ከተማ አስተዳደር ከ400 ሚሊየን ብር በላይ በሆነ ወጪ ያስገነባቸውን የተለያዩ ፕሮጀክቶች አስመረቀ፡፡

የክፍለ ከተማ አስተዳደሩ በ2014 በጀት ዓመት ለተለያዩ አገልግሎቶች የሚውሉ 47 ፕሮጀክቶች ተጠናቅቀው ለአገልግሎት ዝግጁ መሆናቸው ተገልጿል፡፡

በዚህም በትምህርት ዘርፍ 19 የመማሪያ ክፍሎች እና የአስተዳደር ሕንፃዎች፣ 7 የስፖርት ማዘውተሪያ እና የወጣቶች ስብእና መገንቢያ ማዕከላት፣ በሕክምና ዘርፍ 1 ላቦራቶሪ እና የመድኃኒት አገልግሎት መስጫ ተቋም፣ የቤተ መፃሕፍት ግንባታና እድሳት፣ በሥራ ዕድል ፈጠራ ዘርፍ የ27 ሼዶች ግንባታና እድሳት ሥራዎች ተጠናቀዋል ነው የተባለው።

በኅብረተሰብ ተሳትፎ 54 ፕሮጀክቶች የተጠናቀቁ ሲሆን የ21 ኪሎ ሜትር የኮብልስቶን መንገድ ሥራ፣ የ28 ኪሎ ሜትር የፍሳሽ ማስወገጃ ቱቦዎችና ካልቨርት ሥራ እንዲሁም የ5 የማኅበረሰብ አቀፍ የፖሊስ ማዕከላት ግንባታ ይጠቀሳሉ።

በክፍለ ከተማው ሥር ያሉ ወረዳዎችን ተደራሽ በማድረግ በመንግሥት ወጪና በኅብረተሰብ ተሳትፎ አማካይነት ከ101 ያላነሱ ፕሮጀክቶች በ403 ሚሊየን ብር ወጪ ተገንብተዋልም ነው የተባለው።

ክፍለ ከተማው በኅብረተሰብ ተሳትፎ የተለያዩ መሠረተ ልማቶችን በመገንባት ለአገልግሎት ዝግጁ ያደረገ ሲሆን በ60 እና በ90 ቀናት ሰው ተኮር ተግባራት ዕቅድ መሠረትም የተለያዩ አጋር አካላትን በማሳተፍ ግንባታቸው ሲከናወኑ የቆዩ ፕሮጀክቶች ናቸው የተመረቁት፡፡

የፕሮጀክቶቹ የምረቃ ሥነ ሥርዓት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባ ጃንጥራር አባይ፣ የክፍለ ከተማ ዋና ሥራ አስፈፃሚ አለምፀሐይ ሺፈራው እንዲሁም ሌሎች የሥራ ኃላፊዎች በተገኙበት ተከናውኗል።

በሰለሞን በየነ

ለፈጣን መረጃዎች፦
ፌስቡክ https://bit.ly/3Ma7QTW