ሐምሌ 10/2013 (ዋልታ) – የቦንጋ መምህራን ትምህርት ኮሌጅ በዲፕሎማ መርኃግብር ያሰለጠናቸውን 817 ዕጩ መምህራን በዛሬው እለት አስመርቋል።
የኮሌጁ ዲን አንተነህ አየለ ባደረጉት ንግግር ተመራቂዎች በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ሳይደናቀፉ ለዚህ ቀን በመብቃታቸው የእንኳን ደስ ያላችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል።
የተገባደደው የትምህርት ዘመን የፈተና፣ የስጋት በመጨረሻም የስኬት ማሳያ ሆኖ ማለፉንም አቶ አንተነህ ጠቁመዋል።
ተመራቂዎች ወደ መምህርነት ሙያው በሚሰማሩበት ወቅትም ሃገርና ህዝብ የጣለባቸውን ትውልድን የማነፅና የመቅረፅ ኃላፊነት በአግባቡ እንዲወጡ አሳስበዋል።
የኮሌጁ ምክትል ዲን እና የመምህራን ልማት ዳይሬክተር ዶ/ር አህመድ እስማኤል በበኩላቸው፣ ኮሌጁ ከተመሰረተበት 1991 ዓ.ም አንስቶ በመደበኛና ተከታታይ የሥልጠና መርኃግብሮች ከ33 ሺህ 600 በላይ መምህራን ማሰልጠኑን ገልፀዋል።
በ2013 ዓ.ም የትምህርት ዘመንም በ23 የትምህርት ክፍሎች ያሰለጠናቸውን 817 ዕጩ መምህራን በዲፕሎማ መርኃግብር ማስመረቁን ተናግረዋል።
ኮሌጁ በቀጣናው በሚገኙ የአፍ መፍቻ ቋንቋዎች ልማት ላይ እየሰራ ሲሆን፣ በዘንድሮው የትምህርት ዘመንም በካፊ ኖኖ፣ በሸኪ ኖኖ፣ በቤንች ኖን እና በሸኮ ኖጎ ቋንቋዎች አሰልጥኖ ማስመረቁ ተገልጿል።
(በነስረዲን ኑሩ)