የተለያዩ ህገወጥ ጦር መሣሪያዎች ከነተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር ዋሉ

ጥር 20/2014 (ዋልታ) የአዲስ አበባ ፖሊስ እና የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት በጋራ በመቀናጀት ባደረጉት ኦፕሬሽን አንድ ስናይፐር ጠብመንጃ፣ ከ20 ሺሕ በላይ የክላሽ እና 260 የብሬን ጥይት ከእነ ተጠርጣሪዎቹ መያዛቸውን አስታወቁ፡፡
ህገ-ወጥ የጦር መሳሪያ ዝውውርን ለመቆጣጠር እየተሰራ ያለው ሥራ ተጠናክሮ መቀጠሉን ፖሊስ አስታውቋል፡፡
በኤፍ .ኤስ አር አይሱዙ የጭነት ተሽከርካሪ አካል ላይ መሸሸጊያ በማሰራት ከወሊሶ ወደ አዲስ አበባ ሲጓጓዝ የነበረ አንድ ስናይፐር ጠብመንጃ፣ 20 ሺህ 630 የክላሽን -ኮቭ ጠብመንጃ እና 260 የብሬን ጥይት ጥር 20 ቀን 2014 ዓ.ም በአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ ወረዳ 4 ልዩ ቦታው እህል በረንዳ ተብሎ በሚጠራው አካባቢ የብሔራዊ መረጃና ደኅንነት አገልግሎት እና የአዲስ አበባ ፖሊስ በመተባበር ባከናወኑት ኦፕሬሽን በቁጥጥር ስር እንዳዋሉ ነው የተገለፀው፡፡
ህገ-ወጥ የጦር መሳሪያዎቹን ሲያዘዋውሩ የተገኙ የመኪናው ሾፌርና የጦር መሳሪያውን ያስጫነው ግለሰብ በቁጥጥር ስር ውለው ምርመራው መቀጠሉን የአዲስ አበባ ፖሊስ መረጃ አመላክቷል፡፡