የተባበሩት መንግስታት የልማት ፕሮግራም ለትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ድጋፍ አደረገ

የካቲት 04/2013 (ዋልታ)- በተባበሩት መንግስታት የልማት ፕሮግራም (UNDP) ለትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር የተሽከርካሪ፣ የቢሮ እና የፅህፈት መሳሪያዎች እንዲሁም የተለያዩ መሳሪያዎችን ድጋፍ ማድረጉ ተገልጿል፡፡

የተባበሩት መንግስታት የልማት ፕሮግራም እና የገንዘብ ሚኒስቴር ከትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ጋር ውይይት አድርገዋል፡፡

የገንዘብ ሚኒስትር ዴኤታ ያስሚን ወሀብሬቢ እና የተባበሩት መንግስታት የልማት ፕሮግራም (UNDP) የአፍሪካ ዳይሬክተር በአሁና ኢዚአኮንዋ የተመራ ልዑካን ቡድን በመቐለ ጉብኝት አድርጓል፡፡

ልዑካን ቡድኑ የአንድ ቀን ጉብኝት ያደረገ ሲሆን፣ በትግራይ ስላለው ወቅታዊ ሁኔታ ከትግራይ ጊዜያዊ አስተዳደር ዋና ስራ አስፈፃሚ ከዶ/ር ሙሉ ነጋ እና ከሌሎች የጊዜያዊ አስተዳደሩ ባለስልጣናት ጋር ውይይት ማድረጉን ከገንዘብ ሚኒስቴር ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡