የተባበሩት መንግስታት ጠቅላላ ጉባኤ በኢትዮጵያ ያለውን ወቅታዊ ሁኔታ በትክክል ማስገንዘብ ያስቻለ መሆኑ ተገለጸ

መስከረም 19/2015 (ዋልታ) 77ኛው የተባበሩት መንግስታት ጠቅላላ ጉባኤ በሰሜን ኢትዮጵያ ያለውን ወቅታዊ ሁኔታና የመንግስትን አቋም ለአለም አቀፉ ማህበረሰብ በትክክል ማስገንዘብ ያስቻለ መሆኑ ተገለጸ፡፡
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር መለሰ አለም በሳምንቱ የተከናወኑ ዲፕሎማሲያዊ ሁነቶችን አስመልክቶ ለመገናኛ ብዙኃን ማብራሪያ ተሰጥተዋል ።
ቃል አቀባዩ 77ኛው የተባበሩት መንግስተ ጉባኤ ላይ የኢትዮጵያ አቋም ለአለም አቀፉ ማህበረሰብ ማሳወቅ ያስቻለ ነው ብለዋል።
ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን 20 ከሚደርሱ የተለያዩ ሀገራት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች እንዲሁም አለም አቀፍ ተቋማት መሪዎች ጋር የጎንዮሽ ውይይት ማድረጋቸውንም ገልጸዋል፡፡
በጠቅላላ ጉባኤው በኢትዮጵያ ስለተከናወነው የአረንጓዴ አሻራና የሰቆጣ ቃልኪዳን ፕሮጀክት በስፋት ገለጻ መደረጉንም ተገልጿል።
በመስከረም ቸርነት