የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ የኢትዮጵያ ሉአላዊነት አደጋ ላይ በወደቀ ወቅት ከጎናችን ነበረች ₋ አፈጉባኤ አገኘሁ ተሻገር

የካቲት 28/2014 (ዋልታ) የተባበሩት አረብ ኤምሬትስ የኢትዮጵያ ሉአላዊነትን የውስጥና የውጭ ሃይሎች አደጋ ላይ ለመጣል ባሰፈሰፉበት ወቅት ከጎናችን ነበረች ሲሉ የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈጉባኤ አገኘሁ ተሻገር ገለጹ፡፡

አፈጉባኤው ከተባበሩት አረብ ኢምሬትስ የፌዴራል ብሔራዊ ምክር ቤት አፈጉባኤ ሳክር ሆባሽ ጋር ተወያይተዋል::

በውይይታቸውም የሁለቱ ሀገራት በባህል፣ በታሪክ፣ በሳይንስና ቴክኖሎጂ፣ በቱሪዝም እና በሌሎች መስኮች የቆየ፣ ጠንካራና መልካም ግንኙነት እንዳለቸው ገልጸዋል፡፡

የኢትዮጵያ ሉአላዊነትን አደጋ ላይ በነበረበት ወቅትም ከኢትዮጵያ ጎን ከቆሙት ጥቂት ሀገራት መካከል አንዷ የተባበሩት አረብ ኢምሬትስ መሆኗን አስታውሰው፤ ለዚህም የኢትዮጵያ ሕዝብና መንግስት ሁልጊዜም ከፍ ያለ ምስጋና አለው ብለዋል::

አፈጉባኤ ሳክር ሆባሽ በበኩላቸው ብዙ ሀገራት የተለያዩ ተግዳሮቶች በታሪካቸው የገጠማቸው ሲሆን ኢትዮዽያ በቅርቡ የገጠማት ችግር አንዳንድ ሀገራት በታሪካቸው ከገጠማቸው የተለየ አይደለም ብለዋል::

በተለይም የኢትዮጵያን ሁኔታ ውስብስብ መስሎ እንዲታይ ለማድረግ የሞከሩት አንዳንድ ሀገራት የራሳቸው እሳቤና አመለካከት ለሁሉም ሀገራት በተመሳሳይ መልኩ ያገለግላል ከሚል ከተሳሳተ ድምዳሜ የሚመነጭ ነው ብለዋል::

ከዚህም በተጨማሪም አፈጉባኤ ሳክር ሆባሽ የጠነከረችና የግዛት አንድነቷ የተጠበቀ ኢትዮጵያ እንድትቀጥል የሕዝባቸውና የመንግስታቸው ፅኑ አቋም መሆኑን መግለጻቸውን የምክር ቤቱ መረጃ ያመለክታል::