የተፈናቀሉ ዜጎችን ለማቋቋም ከአንድ ቢሊዮን ብር በላይ ተሰበሰበ

ጥቅምት 30/2014 (ዋልታ) – የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የሀገር መከላከያንና አሸባሪው የህውሃት ቡድን በከፈተው ጦርነት የተፈናቀሉ ዜጎችን ለማቋቋም በተካሄደው የገቢ ማሰባሰባ መርሐግብር አንድ ቢሊዮን 540 ሚሊዮን 732 ሺህ ብር መሰብሰብ ተችሏል።

በገቢ ማሰባሰብ መርሐግብር ጠቅላይ ሚንስትር ዶ/ር ዐብይ አሕመድ፣የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ አዳነች አቤቤ፣ የሀገር መከላከያ ሰራዊት የሰራዊት ግንባታ ስራዎች አስተባባሪ ሌተናል ጀነራል ባጫ ደበሌ፣ የኢፌዴሪ ሀገር መከላከያ ሚኒስትር ዶ/ር አብረሃም በላይ፣ የሀይማኖት አባቶችና ባለሃብቶች ተሳትፈዋል ።

በአንድ ጀምበር ከተሰበሰበው ከአንድ ቢሊዮን 540 ሚሊዮን 732 ሺህ ብር የኢትዮጵያ ባንኮች ማህበር አንድ ቢሊዮን 23 ሚሊዮን 581 ሺህ ብር ድጋፍ ያደረገ ሲሆን ቀሪውን በከተማዋ የሚገኙ ባለሀብቶች ፣ የተለያዩ መንግስታዊና መንግስታዊ ያልሆኑ ተቋማት እንዲሁም ግለሰቦች መለገሳቸውን ከአዲስ አበባ ኮሙዩኒኬሽን ቢሮ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።