የቱሪዝም መስህቦች ማስተዋወቅን ያለመ የጎዳና ላይ ሩጫ ተካሄደ

መስከረም 30/2014 (ዋልታ) የቱሪዝም መስህቦችን ማስተዋወቅን ያለመ የ5ኪሎ ሜትር የጎዳና ላይ ሩጫ በባሌ ዞን ሮቤ ከተማ ተካሄደ።
‘መንገዶች ሁሉ ወደ ባሌ’ በሚል መሪ ሃሳብ የተካሄደው የጎዳና ላይ ሩጫ ውድድሩ አትሌቶችን ጨምሮ ከ3 ሺህ በላይ ሰዎች ተሳታፊ ሆነዋል።
የኦሮሚያ ቱሪዝም ኮሚሽን እና በሳዲያ መልቲ ሚዲያ ትብብር ሲሆን የ2014 ዓ.ም ‘ወይዘሪት ቱሪዝም ኦሮሚያ’ የቁንጅና ውድድር አሸናፊዋ ሃሊማ አብዱልሸኩርን ጨምሮ በርካታ እንግዶች ታድመዋል።
የሮቤ ከተማ ከንቲባ አቶ ገዛኸኝ ደጀኔ በበርካታ የቱሪዝም መስህብነቷ የምትታወቀውን ባሌ የቱሪዝም መስህብ በተለያየ መንገድ ማስተዋወቅ የአካባቢውን የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ ያነቃቃል ብለዋል።
የኦሮሚያ ቱሪዝም ኮሚሽን ተወካይ አቶ ፍጹም ካሳሁን በበኩላቸው “የክልሉን የቱሪዝም መስህቦች በማስተዋወቅ የዘርፉን ተጠቃሚነት ለማሳደግ ይሰራል” ብለዋል።
በዞኑ ለ3ኛ ጊዜ የተዘጋጀው የጎዳና ላይ ሩጫም የዚሁ ጥረት ማሳያ እንደሆነ ኢዜአ ዘግቧል።