የቱሪዝም ዘርፉ ለኢኮኖሚው የሚያደርገውን አስተዋጽኦ ለማሳደግ የተሰራው ሥራ ውጤት እያስመዘገበ ነው

የቱሪዝም ሚኒስትር አምባሳደር ናሲሴ ጫሊ


ሰኔ 7/2016 (አዲስ ዋልታ) በኢትዮጵያ የቱሪዝም መዳረሻዎች የሀገሪቱን የኃብት መፍጠሪያ አማራጭ እንዲሆኑ እየተሰራ ያለው ሥራ ውጤት እየተመዘገበበት መሆኑን የቱሪዝም ሚኒስትር አምባሳደር ናሲሴ ጫሊ ተናገሩ።

የበጀት ዓመቱ የመጨረሻ የ100 ቀናት አፈጻጸም ግምገማ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር) በተገኙበት ተካሂዷል።

በመድረኩ ሰፊ ውይይት ከተደረገባቸው ጉዳዮች መካከል አንዱ የቱሪዝም ዘርፉ መሆኑን አምባሳደር ናሲሴ ጫሊ ተናግረዋል።

በኢትዮጵያ የቱሪዝም ዘርፉ ለኢኮኖሚው የሚያደርገውን አስተዋጽዖ ለማሳደግ የተሰራው ሥራ ውጤት እያስመዘገበ መሆኑንም ጠቁመዋል።

በውጭ ሀገር የቱሪዝም ፍሰቶችን የማስተዋወቅና የሀገር ውስጥ ጎብኚዎችን ቁጥር ለመጨመር እንዲሁም መዳረሻዎችን የማስፋትና ነባሮችን የማደስ ሥራ ለውጤቱ መገኘት አስተዋጽኦ እንዳደረገ ተናግረዋል።

በተለይ አዳዲስ የቱሪስት መዳረሻዎችን መገንባትና ነባሮችንም ዘመኑ በሚጠይቀው ልክ በማደስ ለገበያ ክፍት በማድረጉ ዘርፉ የውጭና የሀገር ውስጥ ጎብኚዎችን ቀልብ በመሳብ ላይ ናቸው ሲሉም አክለዋል።

የኮንፍረንስ ቱሪዝም በማስፋፋት ረገድ ባለፉት አስር ወራት በጤና፣ በትምህርት፣ በማኑፋክቸሪንግና በሌሎችም ዘርፎች አለም ዓቀፍ ስብሰባዎች እንዲካሄዱ በማመቻቸት ገቢን የማሳደግ ሥራ መሰራቱን አብራርተዋል።

በርካታ የገበታ ለሀገር ፕሮጀክቶች ወደ ሥራ መግባታቸውና የገበታ ለትውልድ ሥራዎችን በመጀመር የዘርፉን እድገት ለማፋጠን ተሰርቷል ብለዋል።

በሀገሪቱ የቱሪስት መዳረሻዎች ስታንዳርድ ተዘጋጅቶ ወደ ሥራ ሊገባ መሆኑን ጠቅሰው ይህም ነባር የቱሪስት መዳረሻዎች ገበያው በሚፈልገው ልክ እንዲሆኑ ያደርጋል ነው ያሉት።

ባለፉት 100 ቀናት በሀገሪቱ ተወዳዳሪ ሆቴሎች እንዲኖሩ ደረጃዎችን የመመደብ ሥራ መሰራቱንም ሚኒስትሯ አክለዋል።

ባለፉት አስር ወራት የሀገር ውስጥና የውጭ ጎብኚዎችን ቁጥርና ገቢን ለማሳደግ እየተሰራ ያለው ሥራ ሚኒስቴሩ ከያዘው እቅድ አንጻር ውጤታማ እንደነበር አስገንዝበዋል።

ሀገሪቱ ካላት እምቅ አቅምና ፍላጎት አንጻር ብዙ መሥራት እንደሚጠይቅም መናገራቸውን ኢዜአ ዘግቧል።