የቱርሚ-ኦሞ መንገድ የትራንስፖርት አገልግሎት መስጠት ሊጀምር ነው


ሰኔ 25/2013 (ዋልታ) –
የቱርሚ-ኦሞ የመንገድ ግንባታ ፕሮጀክት ስራ ተጠናቆ ሙሉ ለሙሉ የትራንስፖርት አገልግሎት መስጠት ሊጀምር መሆኑን የመንገዶች ባለስልጣን ገለጸ፡፡
56 ነጥብ 71 ኪሎ ሜትር ርዝመት ያለው ይህ መንገድ በአስፋልት ኮንክሪት ደረጃ የተገነባ ሲሆን፣ በአሁኑ ወቅት 97 በመቶ የሚሆነው ስራ ተጠናቆ የማጠቃለያ ሥራዎች እየተከናወኑ ነው ተብሏል፡፡
በ897 ሚሊየን 5 ሺህ 974.6 ወጪ የተገነባው የመንገድ በጀት በኢትየጵያ መንግስት የተሸፈነ ሲሆን፣ መንገዱ በገጠር 10 ሜትር እና በወረዳ 14 ሜትር የጎን ስፋት አለው ተብሏል፡፡
መንገዱ በዋናነት የቱርሚ ከተማን ከካንጋቴ ከተማ ጋር በማገናኘት ጊዜን የቆጠበ የትራንስፖርት አገልግሎት እንዲኖር ያደርጋልም ነው የተባለው፡፡
ከዚህ ቀደም በአካባቢው ህብረተሰብ ላይ በክረምት እና በበጋ ወቅት በአቧራ እና በጭቃ ይደርስባቸው የነበረውን የጤና ችግር እንዲሁም ከፍተኛ የጉዞ እንግልት የሚያስቀር መሆኑ ተገልጿል፡፡
በአካባቢው የሚገኝ የስኳር ፋብሪካ ምርቱን መንገዱን በመጠቀም በቀላሉ ወደ መሀል ሀገር ማጓጓዝ እንዲችል በማድረግ እረገድ ሚናው የላቀ መሆኑም ነው የተገለጸው።
ከጎረቤት ሀገር ኬኒያ ጋር በማስተሳሰር ረገድም ፋይዳው የጎላ ነው ተብሏል።
በአካባቢው የሚገኘውን የቱሪስት መዳረሻ ስፍራን ለማየት ለሚመጡ ቱሪስቶች የመንገዱ መሰራት ምቹ ሁኔታን እንደሚፈጥር ከኢትዮጵያ መንገዶች ባለስልጣን የተገኘው መረጃ አመላክቷል፡፡