የቲውተር ዘመቻው የውጭ ኃይሎች በኢትዮጵያ ላይ ያላቸውን የተሳሳተ እይታ እየለወጠ ነው – ሱልጣን ኢብራሂም

ነሀሴ 22/2013 (ዋልታ) – የቲውተር ዘመቻው የውጭ ኃይሎች በኢትዮጵያ ላይ ያላቸውን የተሳሳተ እይታ እየለወጠ እንደሚገኝ በዘርፉ በንቃት የሚሳተፉት አቶ ሱልጣን ኢብራሂም (ሱልጣን አባጊሳ) ገለጹ።

አቶ ሱልጣን የቲውተር ዘመቻው የውጭ ኃይሎች በኢትዮጵያ የውስጥ ጉዳይ ይዘውት የነበረውን የተሳሳተ እይታ በመለወጥ እውነታውን እንዲረዱት እያደረገ ነው ብለዋል።

የህግ ማስከበር ዘመቻው ከተጀመረ በኋላ አሸባሪው ህወሓት በሀሰት ፕሮፓጋንዳው በኢትዮጵያ ላይ ጫና እንዲደርስ ከፍተኛ ሥራ ሠርቷል።

ኢትዮጵያውያን እንደ ሀገር የተጋረጠባቸውን አደጋ የፖለቲካና ሌሎች ልዩነቶችን ወደ ጎን በመተው በቲውተር ዘመቻው በንቃት በመሳተፍ እውነታውን ለዓለም አቀፉ ማህበረሰብ በማሳወቅ ረገድ ውጤታማ ሥራ እየተሠራ መሆኑን ለአዲስ ዘመን ገልጸዋል።

እንደ አቶ ሱልጣን ገለጻ፣ አሸባሪ ቡድኑ የሐሰት መረጃን በማሰራጨት አለም አቀፉ ማህበረሰብ በኢትዮጵያ ላይ የተሳሳተ እይታ እንዲይዝ የማድረግ ሰፊ ዘመቻ ከፍቶ ነበር።

ይህን እኩይ ድርጊት ኢትዮጵያውያን በአንድ ድምፅ በተመሳሳይ ሰዓት በመናበብ በከፍተኛ ደረጃ በቲውተር በመሠራቱ ውጤት እያስገኘ ነው።

የተለያዩ አደረጃጀቶችን በመፍጠር በኢትዮጵያ በኩል ያለውን እውነታ ለማሳወቅ በከፍተኛ ደረጃ መሠራቱን የጠቆሙት አቶ ሱልጣን፤ የተለያዩ ቡድኖች ተፈጥረው (click and tweet) በሚል መርሐ ግብር መልዕክቶችን በመቅረጽ መረጃው የሚመለከታቸው አካላት በቀጥታ እንዲደርሳቸው የማድረግ ተግባር እየተከናወነ ነው ብለዋል።