የታርጫ ከተማ የንጹህ መጠጥ ውሃ ፕሮጀክት የመሠረት ድንጋይ ተቀመጠ

ግንቦት 14/2013 (ዋልታ) – የደቡብ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳድር አቶ እርስቱ ይርዳ በዳውሮ ዞን በ205 ሚሊየን ብር ግንባታው የሚጀመረውን የታርጫ ከተማ የንጹህ መጠጥ ውሃ ፕሮጀክት የመሠረት ድንጋይ አኖሩ።
የደቡብ ብልጽግና ፓርቲ ጽ/ቤት ሀላፊ አቶ ጥላሁን ከበደ እና ሌሎች ከፍተኛ የስራ ሀላፊዎች በተገኙበት ነው በዳውሮ ዞን በ205 ሚሊየን ብር የሚገነባውን የታርጫ ከተማ የንጹህ መጠጥ ውሃ ፕሮጀክት የመሠረት ድንጋይ የማኖር ስነ ስርአት የተካሄደው።
ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ እና በዕርሳቸው የተመራው ልኡክ በዳውሮ ዞን ታርጫ ከተማ ሲደርሱ ህብረተሰቡ ደማቅ አቀባበል አድርጎላቸዋል።
ህብረተሰቡ የታርጫ ከተማ የንጹህ መጠጥ ውሃ ችግር አሳሳቢ እንደነበር ከዚህ ቀደም ለምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ ጥያቄ አቅርቦላቸው ነበር ።
የታርጫ ከተማ ነዋሪዎች እንደገለጹት የህዝቡን የንጹህ መጠጥ ውሃ ጥያቄ መነሻ በማድረግ የክልሉ መንግስት ለሰጠው ፈጣን ምላሽ ምስጋና አቅርበዋል::
ምክትል ርዕሰ መስተዳድሩ በዞኑ ከህዝብ ተወካዮች ጋር ውይይት ያደርጋሉ ተብሎ ይጠበቃል።
(ምንጭ፦ የደቡብ ኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ቢሮ)