የትሕነግ ሽብር ቡድን የበቀል ርምጃ ለመውሰድ በአፋር አብአላን ንፁሀን ዜጎችን ገድሏል

ታኅሣሥ 16/2014 (ዋልታ) ከአፋር እና ከአማራ ክልል ተቀጥቅጦ የወጣው የትሕነግ ሽብር ቡድን የበቀል ርምጃ ለመውሰድ በአፋር አብአላ በከፈተው አዲስ ግንባር በኩል ንፁሀን ዜጎችን ገድሏል፡፡
የክልሉ መንግሥት ባወጣው መግለጫ አሸባሪው ይዟቸው ከነበሩት የአፋርና የአማራ ክልል አካባቢዎች ሽንፈትን ተከናንቦ ሲወጣ ሽንፈቱን ለመሸፋፈን በአፋር ክልል ኪልበቲ ረሱ ዞን አብአላ ወረዳ በንፁሀን ላይ ከባድ መሳሪያ በመተኮስ እኩይ ተግባሩን ዳግም በአፋር ሕዝብ ላይ አሳይቷል ብሏል።
የሽብር ቡድኑ በተደጋጋሚ እየተኮሰ ባለው የከባድ መሳሪያ ሴቶች፣ ህፃናትና አዛውንቶችን ለሞት፣ ለአካል ጉዳትና ስደት ዳርጓል፤ በዚህም ቡድኑ ቀንደኛ የአፋር ሕዝብ ጠላት መሆኑን በድጋሚ አረጋግጧል ነው ያለው።
ቡድኑ ሰላም ፈላጊ በመምሰል በመገናኛ ብዘኃን እንደሚዋሸው ሳይሆን በአፋር ክልል በኪልበቲ ረሱ ዞን በኩል አዲስ ግንባር በመክፈት ጭፍጨፋውን ቀጥሏል ሲልም አሳውቋል።
በድኑ ከእስከዛሬው በባሰ መልኩ አብአላ ከተማን በመድፍ በመደብደብ የሰው ህይወት በአሰቃቂ ሁኔታ እንዲጠፋና የግለሰቦች እና የሕዝብ አገልግሎት መስጫ ቦታዎች ላይ ትልቅ ውድመት እንዲደርስ እያደረገ ነው ብለዋል።
ቡድኑ የአፋርን መሬት ወደ ታላቋ ትግራይ የምንከልልበት ሥራዬ ተደናቀፈ በማለት በአፋር ሕዝብ ላይ ጦርነት በማወጅ በርካታ ሰብኣዊ እና ቁሳዊ ኪሳራን ማድረሱንም ግልፅ አድርጓል፡፡
ይሁንና ኢትዮጵያን ካላፈረስኩ ብሎ ለሚዋትተው የሽብር ቡድን ‹‹የምድር ድሮኖቹ (የአፋር ሕዝባዊ ኃይል) ተገቢውን ምላሽ እንደሚሰጡት›› አሳውቋል፡፡