የትምህርት ሚኒስቴርና ኢትዮ ቴሌኮም የወደሙ ትምህርት ቤቶችን መልሶ ለማቋቋም የገቢ ማሰባሰቢያ ስምምነት ተፈራረሙ

የካቲት 3/2014 (ዋልታ) “ኑ የፈረሰውን የትውልድ ማፍሪያ ተቋም መልሰን እንገንባ” በሚል ትምህርት ሚኒስቴር እና ኢትዮ ቴሌኮም በአጭር የፅሁፍ መልዕክት ገቢ ለማሰባሰብ የሚያስችል ስምምነት ተፈራረሙ።

በዚህም የትምህርት ሚኒስትር ብርሃኑ ነጋ (ፕ/ር) የወደሙትን የትምህርት ተቋማት ወደ ነበሩበት መመለስ ሳይሆን በፊት ከነበሩበት የተሻለ ደረጃ ለማድረስ እንሰራለን ብለዋል።

በአጠቃላይ ከወደሙ ትምህርት ቤቶች ውስጥ 3 ሺሕ 300 የሚሆኑትን ትምህርት ቤቶች የወደሙባቸው ክልሎች የሚጠግኗቸው መሆኑን እና ቀሪዎቹን ግን ከአጋር አካላት ጋር በትብብር እንደሚሰራ ነው ሚኒስትሩ የገለፁት።

የኢትዮ ቴሌኮም ዋና ሥራ አስፈፃሚ ፍሬህይወት ታምሩ በበኩላቸው የወደመውን የአገር ሀብት እና የትውልድ ማፍሪያ ትምህርት ቤት በአጭር የፅሁፍ መልዕክት 9222 ላይ እና በቴሌ ብር አማካኝነት የበኩላችንን እንወጣ ነው ያሉት።

በሜሮን መስፍን