የትምህርት ሚኒስትሩና የአዲስ አበባ ከንቲባ የ12ኛ ክፍል ፈተና አሰጣጥ ሂደትን ጎበኙ

የ12ኛ ክፍል ፈተና አሰጣጥ ሂደት

ጥቅምት 29/2014 (ዋልታ) የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤና የትምህርት ሚኒስትሩ ብርሃኑ ነጋ (ፕ/ር) በከተማዋ የ12ኛ ክፍል ፈተና አሰጣጥ ሂደትን ተዘዋውረው ተመለከቱ፡፡

በአዲስ አበባ በ62 የፈተና ጣቢያዎች የሚሰጠው የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ብሔራዊ ፈተና በዛሬው ዕለት ተጀምሯል።

ፈተናው ከሚሰጥባቸው 62 ጣቢያዎች መካከል ኮከበ ጽበሀ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት እና እቴጌ መነን የልጅ አገረዶች አዳሪ ትምህርት ቤት የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አዳነች አቤቤ፣ የትምህርት ሚኒስትር ብርሃኑ ነጋ (ፕሮፌሰር) እና የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ትምህርት ቢሮ ኃላፊ ዘላለም ሙላቱ ተገኝተው የፈተናውን ሂደት ተመልክተዋል።

የከተማ አስተዳደሩ ከንቲባ አዳነች አቤቤ የፈተና ሂደቱን አስመልክቶ በሰጡት አስተያየት በአዲስ አበባ ደረጃ በ62 የፈተና ጣቢያዎች 36 ሺሕ 401 ተማሪዎች ፈተናውን ለመውሰድ መመዝገባቸውንና ተማሪዎቹም ፈተናውን ሰላማዊ በሆነ ሁኔታ በመፈተን ላይ እንደሚገኙ መመልከታቸውን ገልጸዋል፡፡

የፀጥታ አካላትም ኃላፊነታቸውን በአግባቡ በመወጣት ላይ እንደሚገኙ ማረጋገጣቸውን የጠቆሙት ከንቲባዋ ፈተናውን ለሚወስዱ ተማሪዎችም መልካም ውጤት እንዲገጥማቸውና ቀጣዩ የህይወት ምዕራፋቸው ስኬታማ እንዲሆን ተመኝተዋል።

የኢፌዴሪ ትምህርት ሚኒስትር ብርሃኑ ነጋ (ፕ/ር) በበኩላቸው በመላ ሀገሪቱ 617 ሺሕ ተማሪዎች ለመፈተን መመዝገባቸውንና ከተመዘገቡ ተማሪዎች መካከል 91.5 በመቶ የሚሆኑት በዛሬው ዕለት ፈተናውን በመውሰድ ላይ እንደሚገኙ ገልጸዋል፡፡

ፈተናውን በተለያዩ ምክንያቶች ያልወሰዱ ተማሪዎች በአንድ ወር ውስጥ እንዲፈተኑ እንደሚደረግ በመጥቀስ ሀገሪቱ በዚህ አይነት የፀጥታ ችግር ውስጥ ሆና ፈተናው ሰላማዊ በሆነ ሁኔታ መካሄድ መጀመሩ ጠንካራ ሀገር መሆኗን እንደሚያሳይ ማስገንዘባቸውን ከከተማ አስተዳደሩ ትምህርት ቢሮ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።