የትምህርት ጥራት እና የሀገር ዕድገት ምን አገናኛቸው?

የትምህርት ጥራት እና የሀገር ዕድገት ምን አገናኛቸው?
በፍፁም ሳልህ

ጥቅምት 11/2015 (ዋልታ) አሁንም መማር፣ መማር፣ መማር፤ የሚለው የቭላዲሚር ሌኒን ጥቅስ ጊዜም የማይሻር ጥቅስ ነው። የትኛውም ሥርዓት ቢሆን ይህንን ጥቅስ ደጋግሞ ማለቱ አይቀርም። ምክንያቱም ትምህርት የጥበብ መጀመሪያ ነውና። ይህ ጥቅስ በራሱ የትምህርት ፍልስፍና ነው።

የትምህርት ፍልስፍና ስንመለከት ዜጎች በራሳቸው የሚተማመኑ፣ ብቁና በምክንያታዊ ትንተና የሚያምኑ፣ በሙያቸው ብቃት ያላቸው፣ ሥራ ፈጣሪዎች፣ አዳዲስ ግኝቶችን አፍላቂዎች፣ ጠንካራ የሥነ ምግባርና ግብረገባዊ እሴቶችን የተላበሱ፣ ለሕግ ዘብ የቆሙ፣ በዓለም አቀፍ ገበያ ተወዳዳሪና ብቁ ዜጋ ሆነው አጠቃላይ ሰብእናቸው የተገነባ ዜጎችን በማፍራት ብዝኃነትን ላካተተው አገራዊ አንድነትና ሠላም ዘብ እንዲቆሙ ማድረግ ነው። ይህ ደግሞ በትምህርት ነው የሚገኘው።

አንዲት ሀገር ሁለንተናዊ እድገትን በማምጣት የሕዝቦቿን ኑሮ ማሳደግ የምትችለው በሚኖራት የሰው ኃይል እምቅ አቅም ነው፡፡ ዛሬ በሣይንስና ቴክኖሎጂ በልጽገው በአገራቸው ልማትን በማምጣት የሕዝባቸውን ተጠቃሚነት ያጎለበቱ አገራት ልምድ የሚያሳየን ይህንኑ ሐቅ ነው፡፡ ለዚህ ማሳያ በቅርብ ዓመታት ከነበሩበት የድህነት አረንቋ ወጥተው ከፍተኛ የሣይንስና ቴክኖሎጂ እድገት ደረጃ ላይ የደረሱ እንደ ደቡብ ኮሪያ፣ ቻይና፣ ሲንጋፖር፣ ቬትናም፣ ማሌዢያ፣ ወዘተ. ያሉ አገራት ተሞክሮን መጥቀስ ይቻላል፡፡

እነዚህ አገራት ለትምህርትና ሥልጠና በሰጡት ትኩረት የሰው ኃይል ሀብታቸውን በከፍተኛ ደረጃ በማልማት ከፍተኛ ሀገራዊ እድገት አስመዝግበዋል፡፡ የሕዝባቸውን ኑሮ ማሻሻል ችለዋል፡፡ አገራቱ የአይሲቲ (Information, Communication and Technology) ፖሊሲ ቀርፀው ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ መስተጋብሮቻቸው ውስጥ በጥብቅ ዲስፒሊን ተግባራዊ በማድረጋቸው በአጠቃላይ ኅብረተሰባቸው ላይ ለውጥ ለማምጣት ችለዋል።

የኢትዮጵያ የትምህርት ፖሊሲም በዋናነት በሥነ ምግባር፣ በመልካም እሴትና በብቃት የታነጸ ዜጋን ለማፍራት በሚያስችል መንገድ የተቀረፀ፣ የሀገሪቱን ዕድገትና አንድነት በሚያስቀጥልና ለሀገር በቀል እውቀቶች ተገቢውን ትኩረት የሰጠ መሆኑን የትምህርት ፖሊሲው ያመለክታል።

በ2010 ዓ.ም በትምህርትና ስልጠና ችግሮችና የመፍትሄ አቅጣጫዎች ላይ የተካሄደ የጥናት ጽሑፍ እንደተገለፀው ትምህርትና ሥልጠና ብቁና በቂ የሰው ኃይል በማፍራት ረገድ ከፍተኛ ድርሻ ያለው በመሆኑ ይህንኑ ዓላማና ግብ ለማሳካት ባለፉት ዓመታት የትምህርት ተደራሽነት፣ ፍትሐዊነት፣ አግባብነትና ጥራት ለማጎልበት ሰፊ ሥራዎች ሲሰሩ ቆይተዋል፡፡

የትምህርትና ስልጠና ፖሊሲውን መሠረት ያደረጉ የትምህርት ስታንደርዶች፣ ስትራቴጂዎችና የትምህርት ልማት መርኃ ግብሮች ከሀገራዊ የልማት አቅጣጫዎች ጋር በማስተሳሰርና በማዘጋጀት ተግባራዊ ተደርገዋል። ሀገር በቀሉ የአስር ዓመት መሪ እቅድ ወጥቶ እየተተገበረ ይገኛል። በዚህም መሠረት በሁሉም ዘርፎች የትምህርትና ሥልጠና ተቋማትን በማስፋፋት የትምህርት ተደራሽነትና ፍትሐዊነት በማጎልበት በኩል በርካታ ሥራዎች እየተሰሩ ናቸው፤ አመርቂ ውጤቶችም እየተመዘገቡ ነው፡፡

እስከ ዛሬ ድረስ ሀገሪቱ በተለያዩ ዘርፎች ያሰለጠነቻቸው ባለሙያዎች ሀገሪቱ አሁን ለደረሰችበት የእድገት ደረጃ የበኩላቸውን አስተዋጽኦ እያበረከቱ ይገኛሉ፡፡ ሆኖም የትምህርትና ሥልጠና ጥራትና አግባብነትን በተመለከተ በሁሉም የትምህርትና ሥልጠና ዘርፎች በተለይ የተማሪዎችን የመማር ውጤት ከማሻሻል አኳያ ችግሮች አሉ።

የትምህርትና ስልጠና ሥርዓቱ በንድፍ ሀሳብ እንጂ በተግባር፣ ክህሎትና ፈጠራ ላይ ያተኮረ አይደለም። የምዘና ሥርዓቱ እውቀትን ብቻ የሚመዝን ነው። ስራ ፈላጊ እንጂ ስራ ፈጣሪ ትውልድ እየተፈጠረ አይደለም። በዚህ ምክንያት ህብረተሰቡ በትምህርትና ስልጠና ሥርዓቱ የጥራትና የተገቢነት ጥያቄ እያነሳ ይገኛል። ከትምህርት ስልጠናው እውቀት፣ ክህሎት፣ የስራ አመለካከት በበቂ ሁኔታ ይዞ ከመገኘት ይልቅ ትውልዱ ምስክር ወረቀትና ዲፕሎማ ይዞ በመገኘት ዲፕሎማ አምላኪ ሆኗል።

በሂደትም የኩረጃና የኪራይ ሰብሳቢነት አመለካከትና ተግባር ጎልቶ ታይቷል። የምርምርና የቴክኖሎጂ ስራው ጎልብቶ ኢኮኖሚው በሚፈልገው መጠን እያገዘ አይደለም። ሥርዓተ ትምህርቱ የሀገር ፍቅርን፣ ብዝኃነትን፣ የመቻቻልና አብሮ የመኖር፣ ግብረገብነትን ወዘተ እሴቶችን በእውቀት፣ በክህሎትና በአመለካከት በተጨባጭ ማስረፅ ባለመቻሉ ግለኝነት እያየለ፣ ብሄርተኝነት እየገነነ፣ የሀገር ፍቅር እየደበዘዘ እየመጣ ነው። ሀገሪቱ የምትፈልገውን ብቁና በቂ የሰው ኃይል በማፍራት በኩል አሉታዊ ተጽእኖ ነበረው። በመሆኑም እነዚህን ችግሮች በዘላቂነት ለመፍታት ይቻል ዘንድ የትምህርትና ሥልጠና ፍኖተ ካርታ ተዘጋጅቷል።

ትምህርት ሚኒስቴር ነሐሴ 2013 ይፋ ያደረገው የትምህርትና ስልጠና ፍኖተ ካርታ እንዳመለከተው ተማሪዎች አስፈላጊውን የመማር ውጤት (Minimum Learning Competencies) አምጥተው ትምህርታቸውን ማጠናቀቃቸውን ማወቅ፣ ምዘና እውቅትን ብቻ ሳይሆን ክህሎትን፣ አመለካከትን፣ እምቅ አቅምን እንዲመዘን ማድረግ፣ ለዚህ ስኬት ከወረቀት ፈተናዎች በተጨማሪ የምልከታ ክህሎትን፣ ነገሮችን ተንትኖ የማቅረብ ብቃትን፣ በፕሮጀክትና በጽሑፍ ስራዎች አማካይነት መመዘን፣ የትምህርት ምዘና ተከታታይ እንዲሆን ማድረግ የሚሉ ተካተዋል። ስለሆነም ሀገራችን በዓለም አቀፍ ደረጃ ያለችበትን ሁኔታ ለመገምገም እንዲቻል የዓለም አቀፍ ምዘና አባል በመሆን መሳተፍ ስለሚኖርባት መሰረታዊ ክህሎት፣ የህይወት ክህሎትና የከፍተኛ አስተሳሰብ ክህሎት የማይታለፉ ናቸው። እነዚህን ማስተማርና በምዘና ውስጥ ማካተት አስፈላጊና የትምህርት መሰረታዊ ጉዳይ ነው። እነዚህ በሙሉ የትምህርት ጥራትን የሚያረጋግጡ ጉዳዮች ናቸው።

በትምህርትና ስልጠና ፍኖተ ካርታ እንደተገለፀው በዓለም አቀፍ ደረጃ በዚህ ፕሮግራም አገራት ቢያንስ 80 በመቶ አፈጻጸም እንዲኖራቸው እንደ ስታንዳርድ አስቀምጠዋል። የሌሎች አገራትን ልምድ ስናይ በቅርቡ ይፋ በተደረገው የ2017/2018 Global Monitoring Report (GRM) መሠረት ከአፍሪካ አገራ ውስጥ ማላዊ 82 በመቶ፤ ኬኒያ 76 በመቶ ማድረስ ችለዋል፡፡ ስለዚህ ተማሪዎች፣ መምህራን፣ ወላጆች፣ ባለድርሻ አካላትና የሚመለከታቸው በሙሉ ለትምህርት ጥራትና አግባብነት ዘብ የመቆም ሚናቸውን መጫወትና አቅማቸውን ማጎልበት ይጠበቅባቸዋል።

ምዘና እውቀትን ብቻ ሳይሆን ክህሎትን፣ አመለካከትንና እምቅ አቅምን እንዲመዘን ማድረግ በመሆኑ የወረቀትና እርሳስ የማስታወስ ፈተናዎች ወደ ፕሮጀክትና በወቅቱ በሚሰጡ የጽሑፍ ስራዎች ላይ እንዲያተኩር ማድረግ ቀጣይ ስራዎች ሊሆኑ ስለሚገባ ተማሪዎች ጊዜያቸውን በአልባሌ ቦታ ከማሳለፍ ተቆጥበው ትኩረታቸውን ለትምህርት፣ ስልጠናና ጥናት በመስጠት አመርቂ ውጤት ማስመዝገብ ይኖርባቸዋል። ጊዜው የቴክኖሎጂ፣ የሳይንስና የምርምር ጊዜ በመሆኑ ለሀገር ዕድገት መስራት ከሁሉም የሚጠበቅ ተግባር ነው።

የትምህርት ጥራት ደግሞ ለሀገር ዕድገት ያለው ፋይዳ ከፍተኛ መሆኑን ተገንዝበን ከተማሪዎች መማር፣ ማጥናትና መፈተን፣ ከመምህራን በጥራት ማስተማር፣ ከትምህርት አመራር ስትራቴጂካዊ አመራር መስጠት እና ወላጆች የልጆቻቸውን የትምህርት ሁኔታ መከታተል የማይታለፍ ቁልፍ ጉዳዮች ናቸው።

ከላይ በወፍ በረር የተጠቀሱ የትምህርት ሥርዓቱ ሊያጎለምሱ የሚችሉ አበይት ተግባራት ተተግብረው ፍሬ እንዲያፈሩ ዛሬ ላይ ሁላችንም የቤት ስራችንን በአግባቡ እንስራ ለማለት እወዳለሁ፡፡

ለፈጣን መረጃዎች፦
ፌስቡክ https://bit.ly/3Ma7QTW
ቴሌግራም https://t.me/WALTATVEth
ዩቲዩብ https://www.youtube.com/c/WaltaTV/featured
ቲዊተር https://twitter.com/walta_info
አብራችሁን ስለሆናችሁ እናመሰግናለን!