የትራንስፖርት ሚኒስትሯ ከሱዳን አቻቸው ጋር ተወያዩ

በትራንስፖርት ሚኒስትር ወ/ሮ ዳግማዊት ሞገስ የተመራው የልዑካን ቡድን ከሱዳን መሠረተ ልማትና ትራንስፖርት ሚንስትር እንዲሁም ተጠሪ ከሆኑ መስሪያ ቤቶች ጋር የምክክር መድረክ አድርገዋል፡፡

ምክክሩ በዋናነት ከዚህ ቀደም በአገራችን በኩል ፖርት ሱዳንን በመጠቀም ሂደት ያጋጠሙ ችግሮችን  በጋራ በመፈተሽ አፋጣኝ ምላሽ ለመስጠት በሚያስችሉ ተግባራት ዙሪያ ያተኮረ  ነው ተብሏል፡፡

ፖርት ሱዳንን ተጨማሪ የወደብ አማራጭ በማድረግ የአገራችንን የወጪ-ገቢ ንግድ ለማሳለጥና ማዳበሪያን ጨምሮ ሌሎች ምርቶችን በዚሁ ወደብ በመጠቀም ለሰሜንና ምዕራቡ የአገራችን ክፍል ተደራሽ ለማድረግ በሚያስችሉ ሁኔታዎች ዙሪያ ጠቃሚ ውይይት መደረጉ ተገልጿል።

በተጨማሪም  ሚኒስትሯ ከሱዳን ማዕድን እና ኢነርጂ ተጠባባቂ ሚኒስትር ኽይሪ አብዱልራህማን ጋር በማዕድንና ኢነርጂ ዘርፍ በተለይም በነዳጅ ምርቶች አቅርቦትና ስርጭት ዙሪያ ውይይት አድርገዋል።

ከሱዳን ወደ አገራችን የሚገቡ የነዳጅ ምርቶችን ከማጓጓዝ ጋር በተገናኘ እያጋጠሙ በሚገኙ ችግሮች እና  መፍትሄዎቻቸው እንዲሁም በሁለቱ አገራት ሊከናወኑ በሚችሉ የጋራ ፕሮጀክቶች ዙሪያ ተወያይተዋል፡፡

ከሱዳን ወደ አገራችን የሚገባውን የቤንዚን አቅርቦት ለማሻሻል የተጀመሩ ጥረቶችን ለማጠናከር በሚረዱ የትብብር መስኮች ዙሪያም ውይይት መካሄዱን ከትራንስፖርት ሚኒስተር ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።