የትራንስፖርት አገልግሎቱን በሚያስተጓጉሉ አሽከርካሪዎች ላይ እርምጃ እንደሚወሰድ ተገለጸ

ግንቦት 2/2014 (ዋልታ) ከነዳጅ ዋጋ ማስተካከያ ጋር ተያይዞ አገልግሎቱን በተገቢው መንገድ በማይሰጡ የህዝብ ትራንስፖርት አገልግሎት ሰጪዎች ወይም የትራንስፖርት አገልግሎት በሚያቋርጡ ተሽከርካዎችና አሽከርካሪዎች ላይ እርምጃ እንደሚወስድ የአዲስ አበባ ትራንስፖርት ቢሮ አስታውቋል፡፡

የቢሮው የኮሚዩኒኬሽን ጉዳዮች ዳይሬክተር እጸገነት አበበ እንደገለጹት፣ ማንኛውም የህዝብ ትራንስፖርት አገልግሎት ሰጪዎች፣ ሸገር የብዙሃን ትራንስፖርት ድጋፍ ሰጪዎችን ጨምሮ በተመደቡበት የስምሪት መስመር በመገኘት በተቀመጠው የታሪፍ መጠን ብቻ አገልግሎቱን መስጠት ይገባቸዋል፡፡

በጥናት መመለስ የሚገባቸው ጉዳዮች ካሉም ቢሮው አሰራሩን በመፈተሽ በሂደት ምላሽ እሰጣለሁ ብሏል፡፡

በሸገር የብዙሃን ትራንስፖርት አገልግሎት በኪራይ ውል አገልግሎት የሚሰጡ ድጋፍ ሰጪዎች ከቢሮው ጋር በገቡት ውል መሠረት የትራንስፖርት አገልግሎት የማይሰጡትን ቢሮው ከስምምነት ውል ውጪ እንደሚያደርጋቸው አውቀው ወደ ነበሩበት መስመር በፍጥነት እንዲገቡና ስራቸውን እንዲሰሩም ቢሮው ጥሪ ተላልፏል፡፡

ከነዳጅ ዋጋ ጭማሪ ጋር ተያይዞ ህብረተሰቡን ከታሪፍ በላይ በሚያስከፍሉ፣ መስመር በሚያቆራርጡ፣ የመስመር ታፔላ በማይሰቅሉ (ከእይታ ውጪ በሚያደርጉ)፣ ታሪፍ በማይሰቅሉ (በማይለጥፉ)፣ ተሽከርካሪዎችን ከተፈቀደላቸው አገልግሎት ውጪ የሚያውሉ የህዝብ ትራንስፖርት ሰጪ አሽከርካሪዎች ካሉ ከወዲሁ ጥብቅ ጥንቃቄ በማድረግ ስራቸውን በተገቢው መንገድ እንዲያከናውኑ  ጠይቋል፡፡

ቢሮው ህግና መመሪያዎችን ተከትለው በማይሰሩ የህዝብ የትራንስፖርት አገልግሎት ሰጪ አሽከርካሪዎች ላይ የማያዳግም እርምጃ እንደሚወስድ ማስታወቃቸውን ኢቢሲ ዘግቧል፡፡

ህብረተሰቡ ለአላስፈላጊ ወጪና እንግልት እንዳይዳረግ ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋር እንደሚሰራ የአዲስ አበባ ትራንስፖርት ቢሮ አስታውቋል፡፡