የትራንስፖርት አገልግሎት ሰጪ ተሽከርካሪዎች ላይ ወንጀል ሲፈፅሙ የነበሩ ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር ዋሉ

መጋቢት 07/2013 (ዋልታ) – የትራንስፖርት አገልግሎት ሰጪ ተሽከርካሪዎች እና አሽከርካሪዎቻቸው ላይ ወንጀል ሲፈፅሙ የነበሩ ስምንት ተጠርጣሪዎችን በቁጥጥር ስር ማዋሉን የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን አስታወቀ፡፡

ተጠርጣሪዎቹ በአዲስ አበባ በተለያዩ ክፍለ ከተሞች ወንጀሉን ሲፈፅሙ የነበረው የትራንስፖርት አገልግሎት ፈላጊ መስለው ተሽከርካሪ እንዲመጣላቸው ወደ ጥሪ ማዕከል በመደወል እና መንገድ ላይ ሲንቀሳቀሱ ያገኙትን የትራንስፖርት አገልግሎት ሰጪ ተሽከርካሪ በማስቆም መሆኑ ታውቋል፡፡

በዚህም ተጠርጣሪዎቹ ከተሳፈሩ በኋላ ወንጀሉን ለመፈፀም የመረጡት ቦታ ላይ ሲደርሱ እዚያው ከሚጠብቋቸው ሌሎች ግብረ አበሮቻቸው ጋር በመተባበር “ከኋላ የምንጭነው ዕቃ አለ ኮፈኑን ክፈትልን” በማለት አሽከርካሪውን እንዲወርድ ካደረጉ በኋላ ጉዳት አድርሰው ተሽከርካሪውን እና የአሽከርካሪውን ሌሎች ንብረቶች ይዘው ሲሰወሩ ቆይተዋል፡፡

ይህን ተከትሎም የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን የማዕከል የክትትል አባላት ከንፋስ ስልክ ላፍቶ ክፍለ ከተማ ፖሊስ መምሪያ ጋር በመቀናጀት ባደረጉት መረጃ የማሰባሰብ እና የክትትል ስራ የወንጀል ፈፃሚዎቹን በቁጥጥር ስር ማዋል እንደተቻለ ኮሚሽኑ ገልጿል፡፡

በሂደቱም ተጠርጣሪዎቹ 8 ተመሳሳይ ወንጀሎችን መፈፀማቸውን በምርመራ ማረጋገጥ የተቻለ ሲሆን ተሽከርካሪዎቹን ከወሰዱ በኋላ አካላቸውን በታትነው እንደሚሸጡ ተረጋግጧል፡፡

እስካሁን በተገኘው መረጃም ከተወሰዱት 8 ተሽከርካሪዎች መካከል በፖሊስ ክትትል እና በህብረተሰቡ ትብብር ስድስቱ መመለሳቸው ታውቋል፡፡

ከዚህ ጋር ተያይዞ 4 የወንጀሉ ዋና ፈፃሚዎች፣ 2 ባለጋራዦች፣ 1 ደላላ እና 1 የተሽከርካሪዎቹን አካል የሚፈታታ በአጠቃላይ 8 ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር ውለው ምርመራ እየተደረገባቸው መሆኑን የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን አስታውቋል፡፡