የትራንስፖርት ዘርፉን ዘመናዊና ቀልጣፋ ለማድረግ የሁሉም ርብርብ ያስፈልጋል- አቶ ደመቀ መኮንን

የትራንስፖርት ዘርፉን ዘመናዊና ቀልጣፋ ለማድረግ ሁሉም ባለድርሻ አካላት ርብርብ ሊያደርጉ እንደሚገባ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትርና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ገለፁ።

ደመቀ የትራንስፖርት ዘርፍ የ10 ዓመት መሪ የልማት እቅድን ዛሬ በይፋ አስጀምረዋል።

ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩ በዚህ ወቅት እንዳሉት አገሪቱ ካሰበችበት የእድገት ደረጃ ለመድረስና ብልጽግናዋን ለማረጋገጥ የትራንስፖርት ዘርፉን ማዘመን ወሳኝ ነው።

ለዘመነ ቱሪዝም፣ ግብርና እና ሌሎች ስኬቶችን ለማስመዝገብ የትራንስፖርት ዘርፍ እድገት አስፈላጊ መሆኑን ጠቅሰዋል።

ዘርፉ ለሁሉም የልማት ስኬት የጀርባ አጥንት መሆኑን ገልጸዋል።

“ትራንስፖርትን ማዘመን አገርን ማዘመን ነው” ያሉት አቶ ደመቀ መንግስት ይህን ከግምት በማስገባት እየሰራ መሆኑን ገልጸዋል።

ዘርፉን ለማዘመን ከፍተኛ የሀብት ፈሰስ እያደረገ መሆኑንም ነው ያነሱት።

ዘርፉን በይበልጥ ዘመናዊና ቀልጣፋ ለማድረግ የ10 ዓመት መሪ እቅድ መዘጋጀቱን ገልፀው የተጣለበትን ግብ እንዲመታ ሁሉም አካላት ርብርብ እንዲያደርግ ጠይቀዋል።

የልማት እቅዱ የትራንስፖርት መሰረተ ልማትን የማስፋት፣ የተቀናጀ የብዙሃን ትራንስፖርት ተደራሽነትን ለማሳደግና የሎጀስቲክ ትራንስፎርሜሽንን የሚያረጋግጥና የሚያዘመን ግብ አለው ተብሏል።

የትራፊክ ደህንነትና ማኔጅመንትን በከፍተኛ ደረጃ የማሻሻል እንዲሁም የትራንስፖርት ዘርፍ የአየር ንብረት ለውጥ ጋር ተያይዞ የሚመጡ ጫናዎችን ለመቋቋም በሚያስችል መልኩ መዘጋጀቱም ከኢዜአ ያገኘነው መረጃ ያመለክታል።