የትራፊክ አደጋን በሚጠበቀው መጠን መቀነስ አልተቻለም- ቋሚ ኮሚቴው

የትራፊክ አደጋን በሚጠበቀው መጠን መቀነስ አለመቻሉን የከተማ ልማት ኮንስትራክሽን እና ትራንስፖርት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ገለጸ፡፡

በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የከተማ ልማት ኮንስትራክሽን እና ትራንስፖርት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ የፌደራል ትራንስፖርት ባለስልጣንን የ2013 በጀት ዓመት የሁለተኛ ሩብ የዕቅድ አፈጻጸም በገመገመበት ወቅት የትራፊክ አደጋ በሚጠበቀው መጠን ባለመቀነሱ በትኩረት እንዲሰራ አሳስቧል፡፡

የፌደራል ትራንስፖርት ባለስልጣ የወጪና ገቢ ንግዱን በማፋጠን፣ የፍጥነት መገደቢያ መሳሪያ በማስገጠምና የመንገድ ዳር ምልክቶችንና ማመላከቻዎችን በመትከል ጥሩ አፈጻጸም እንደነበረውና በቀጣይም አጠናክሮ መቀጠል እንደሚገባው ቋሚ ኮሚቴው አመላክቷል፡፡

በሌላ በኩል የፕሮጀክቶች አፈጻጸም መጓተት፣ የትራፊክ አደጋን በሚጠበቀው መጠን አለመቀነስ፣ በአዲስ አበባ እና በሀገር አቋራጭ ትራንስፖርት ዘርፍ ያለው እንግልትና የተሽከርካሪዎች ከደረጃ በታች መሆን እንዲሁም፤ ሞዴል የአሽከርካሪ ብቃት ማሰልጠኛዎችን ማብቃት ላይ የሚታዩ ጉድለቶችን በተመለከተ አስተያየት ተሰጥቷል፡፡

የትራንስፖርት ባለስልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ አብዲሳ ያደታ፤ የተጓተቱ ፕሮጀክቶችን በተመለከተ ከወሰን ማስከበርና ተያያዥ ችግሮች ጋር ያለው ችግር ተቀርፎ በአጭር ጊዜ እንደሚጠናቀቁ ገልጸዋል፡፡

የትራፊክ አደጋን ለመቀነስ ከባለፈው 6 ወር አፈጻጸም አንጻር የተሻለ ቢሆንም የአሽከርካሪዎችን ባህሪ ለመለወጥ የሚያስችል ግንዛቤ ከመፍጠር ጀምሮ ስርዓተ ትምህርቱ ውስጥ ገንቢ ይዘቶችን በማካተት ዘላቂ የትውልድ ግንባታ ስራ እየተሰራ መሆኑን ዋና ዳይሬክተሩ መናገራቸውን ከህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ያገኘነው መረጃ ያመለክታል፡፡