የትንሳኤ በዓል መልካምነት አሸናፊ ይሆናል ብለን የምናምንበት ነው – አምባሳደር ኢቭጌኒ ተረክሂን

ሚያዝያ 16/2014 (ዋልታ) “የትንሳኤ በዓል መጪው ጊዜ የተሻለ ይሆናል ብለን ተስፋ የምናደርግበት፤ መልካምነት አሸናፊ ይሆናል ብለን የምናምንበት ነው” ሲሉ በኢትዮጵያ የሩሲያ አምባሳደር ኢቭጌኒ ተረክሂን ገለጹ።
የበዓሉ ደስታ አዳዲስ መልካም ነገሮችን የማድረግ ጅማሬ ነው ብለዋል።
አምባሳደር ኢቭጌኒ ተረክሂን ለሁሉም የኦርቶዶክስ እምነት ተከታዮች “ለትንሳኤው በዓል እንኳን አደረሳችሁ፤ እንኳን ደስ አላችሁ ለማለት እወዳለሁ” ብለዋል።
የትንሳኤ በዓል ደስታ አዳዲስ መልካም ነገሮችን የማድረግ ጅማሬ፣ የተቸገሩትና መርጃ እና በአንድነት ውስጥ ሰላምና መስማማትን መፍጠሪያ መሆኑን ገልጸዋል።
በጋራ ስንሆንና ተመሳሳይ እሴቶች ስንጋራ ሁሉንም ፈተናዎች ማለፍ እንዲሁም ደስታና ብልጽግና ላይ መድረስ እንደምንችል አመልክተዋል።
የትንሳኤ በዓል የሰላም፣ የጤናና የደስታ እንዲሆን አምባሳደር ኢቭጌኒ ተረክሂን መልካም ምኞታቸውን ማስተላለፋቸውን በአዲስ አበባ የሩሲያ ኤምባሲ መረጃ አመላክቷል።