የትግራይ ብልጽግና ፓርቲ ከፍተኛ አመራሮች በአዲግራት ከተማ የደረሰውን ጉዳት ጎበኙ

ዶክተር ሙሉ ነጋ

የትግራይ ብልጽግና ፓርቲ እና የጊዜያዊ አስተዳደሩ ከፍተኛ አመራሮች በአዲግራት ከተማ የህወሃት ጁንታ ያደረሰውን ጉዳት ጎብኝተዋል፡፡

በትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ዋና ስራ አስፈጻሚ ዶክተር ሙሉ ነጋ እና በትግራይ ብልጽግና ፓርቲ ከፍተኛ አመራር ዶክተር አብርሃም በላይ የተመራ ልዑክ በአዲግራት ዩኒቨርሲቲና በአዲስ መድሃኒት ፋብሪካ ላይ የደረሰውን ውድመት ተዘዋውረው ተመልክተዋል።

ዶክተር አብርሃም በላይ

በጉብኝቱ የህወሃት ጁንታ ለህዝብ የማያስብ እና ከህዝብ አብራክ የወጣ የማይመስል የጥፋት ቡድን መሆኑን በመሰረተ ልማቶች ላይ ባደረሰው ጥፋት ማሳየቱ ተገልጿል፡፡

የህወሃት ጁንታ በአዲግራት ዩኒቨርሲቲ ዝርፊያ ከመፈጸም አልፎ የቀረው ንብረት ለመጪው ትውልድ እንዳያገለግል ሰባብሮ እና ከጥቅም ውጪ አድርጎ መፈርጠጡ ተነግሯል።

በአዲግራት ከተማ በሚገኘው አዲስ መድሃኒት ፋብሪካም ተመሳሳይ ድርጊት መፈጸሙ ተገልጿል።

የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ዶክተር ሙሉ ነጋ ቡድኑ በህዝብና በመንግስት ንብረት ላይ የከፋ ጉዳት ማድረሱን ጠቁመዋል፡፡

የቡድኑ የህገወጥ ድርጊት ሰለባ የነበረችው የአዲግራት ከተማ ሰላም በአሁኑ ወቅት እየተመለሰ እንደሆነም ተናግረዋል።

በቀጣይ በትግራይ ክልል አጠቃላይ በህወሃት ጁንታ የደረሱ ጉዳቶች ተጠንተው ለፌዴራል መንግስት ቀርበው መፍትሄ እንዲያገኙ የሚደረግ ስለመሆኑ አመልክተዋል።

የጉብኝት ልዑኩ የአካባቢውን ሰላም ለመጠበቅና የፈረሰውን የመንግስት መዋቅር መልሶ ለማቋቋም ከአዲግራት ከተማ ወጣቶች ጋር ምክክር ማድረጋቸውን ኢዜአ ዘግቧል።

በምክክር መድረኩ በጋራ ለመስራት የሚያስችል መግባባት ላይ ተደርሷል።