የትግራይ ብልጽግና ፓርቲ የመቀሌ ጽህፈት ቤት በይፋ ሥራ ጀመረ

የትግራይ ብልጽግና ፓርቲ

የትግራይ ብልጽግና ፓርቲ በመቀሌ የሚገኘውን የፓርቲውን ዋና ጽህፈት ቤት በይፋ ሥራ አስጀመረ።

በትግራይ ክልል ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች በነጻነት የሚንቀሳቀሱበት ምቹ ሁኔታ መፈጠሩም ተገልጿል።

የትግራይ ብልጽግና ፓርቲ ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ነብዩ ስሑልሚካኤል የጽህፈት ቤቱን ሥራ ማስጀመር አስመልክቶ በሰጡት መግለጫ በህወሓት ቡድን አምባገነንነት የፖለቲካ ፓርቲዎች በትግራይ ክልል ቢሮ ከፍተው መስራት የማይችሉበት ሁኔታ እንደነበር አስታውሰዋል።

ቡድኑ ተወግዶ በትግራይ ክልል ለውጥ በመምጣቱ ብልጽግና ፓርቲን ጨምሮ ሌሎች ህጋዊ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች በነጻነት የሚንቀሳቀሱበት ምቹ ሁኔታ መፈጠሩን ገልጸዋል።

በዚህም ብልፅግና ቢሮውን በመቀሌ ከፍቶ በይፋ ሥራ መጀመሩን ገልጸው፤ “ሌሎች ህጋዊ ፓርቲዎችም በተመሳሳይ መንቀሳቀስ የሚችሉበት እድል ተፈጥሯል” ብለዋል።

በትግራይ ክልል የተጀመረው የለውጥ ምዕራፍ ህዝቡን የሚያሳትፍና ወጣቱን በግንባር ቀደምትነት የለወጡ አራማጅ የሚያደርግ መሆኑንም ተናግረዋል።

ለውጡ በትግራይ ክልል ከዚህ ቀደም የነበሩ የማህበራዊ ፍትህ ችግሮችን የሚፈታ መሆኑን ጠቁመው፤ ለህዝቡ ፍትህን በተጨባጭ የሚያረጋግጥ ሥራ እንደሚሰራም ጠቅሰዋል።

በእውነትና በህብረ ብሔራዊነት በመታገዝ ትግራይን ወደ እውነተኛ ብልጽግና ለማሸጋገር እንደሚሰራም አቶ ነብዩ መግለጻቸውን ከጽህፈት ቤቱ ያገኘነው መረጃ ያመላክታል፡፡